"ሌሎች ሰዎች ስለሚያስቡት ነገር ማሰብ የለብኝም፤ በፈለኩበት ጊዜ እናገራለሁ”- ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ "ተከድቻለሁ" ማለቱ ይታወሳል
ሮናልዶ፤ የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን በዚህ የዓለም ዋንጫ ምርጡ ቡድን ነው ብሏል
የ37 አመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ በቶክ ቲቪ ባደረገው ሰፊ ቃለ ምልልስ ከዩናይትድ እየተገፋ እንደሆነ እንደሚሰማው፣ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግን እንደማያከብር እና የግላዘር ቤተሰብ ለክለቡ ምንም ደንታ እንደሌለው መናገሩ አይዘነጋም፡፡
የቃለ ምልልሱ ማጠንጠኛ በማንቸስተር ቤት የ"ተከድቻለሁ" አይነት ሲሆን ቃለ ምልልሱን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች በመጉረፍ ላይ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡
አስተያየቶቹ በአመዛኙ በሮናልዶ ላይ ያነጣጠሩና ፖርቹጋላዊው ኮከብ ራሱን ከክለብ በላይ አድርጎ ቆጥሯል የሚል ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡
በሮናልዶ ቃለ ምልልስ የተበሳጨው ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድም ቢሆን በተጫዋቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከቀናት በፊት አስታውቋል፡፡
ክለቡ ባወጣው መግለጫ በተጫዋቹ ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ቢገልጽም ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስድ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ለዓለም ዋንጫው ጨዋታ በኳታር የሚገኘው ክርስትያኖ ሮናልዶ ከፒየር ሞርጋን ጋር ካደረገው አነጋጋሪ ቃለ ምልልስ በኋላ ዝምታውን ሰብሯል፡፡
ሮናልዶ በጉዳዩ ላይ በሰጠው ምላሽ ያነሳቸው ሃሳቦችን በተመለከተ ለማንም ማስረዳትና ማረጋገጥ እንደማይጠበቅበት መናገሩን ሮይተርስ ዘገቧል፡፡
ሮናልዶ ቃለ ምልልስ ያደረገው በዓለም ዋንጫ ዋዜማ እንደመሆኑ በፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ሊፈጥረው ስለሚችል ተጽእኖ ተጠይቆም “የፖርቹጋል ቡድን ስኬትን የተራበና አንድ አላማ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ስለዚህ እርግጠኛ ነኝ (ቃለ መጠይቁ) የመልበሻ ክፍሉን ትኩረት አያናውጥም” የሚል ምለሽ ሰጥቷል፡፡
“በሕይወቴ ውስጥ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ ሁል ጊዜ የእኔ ጊዜ ነው” ሲልም ተደምጠዋል የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሮናልዶ።
"ሌሎች ሰዎች ስለሚያስቡት ነገር ማሰብ የለብኝም፤ ስፈልግ እናገራለሁ፡፡ ተጫዋቾቹ ለብዙ አመታት ምን አይነት ሰው እንደሆንኩ በደንብ ያውቁኛል”ም ብሏል፡፡
ሃሙስ ከናይጄሪያ ጋር በነበረው የወዳጅነት ጨዋታ በጨጓራ ችግር ምክንያት ያልተሰለፈው ሮናልዶ ፖርቱጋል ከጋና ጋር በምታደርገው የመጀመርያው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ ጥሩ ስሜት እንደሚሰማው ተናግሯል።
"በጣም ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ነው፣ አገግሜያለሁ እናም በጥሩ ሁኔታ ልምምድ እያደረግኩ ነው እናም የዓለም ዋንጫውን በተቻለው መንገድ ለመጀመር ዝግጁ ነኝ" ሲልም አክሏል።
“ይህ የፖርቹጋል ቡድን አስደናቂ አቅም እንዳለው ይሰማኛል። በእርግጠኝነት ማሸነፍ እንደምንችል አስባለሁ ግን በሚቀጥለው ጨዋታ ላይ ማተኮር አለብን። ስለዚህ ቡድኑ በጋና ላይ እያተኮረ ነው”ም ነው ያለው ሮናልዶ የብሄራዊ ቡድን አጠቃላይ ዝግጅት ሲገልጽ፡፡
የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን በዚህ የዓለም ዋንጫ ምርጡ ቡድን ነው ብሎ እንደሚያምን የተናገረው ሮናልዶ “በመጨረሻ ማን ምርጡ ቡድን እንደሆነ እናያለን” ሲልም በዐለም ዋንጫው ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ስኬት ለማስመዝገብ ያለውን ጉጉት ገልጿል፡፡
ፖርቹጋል በዓለም ዋንጫው ጋና፣ኡራጋይ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡