ክርስቲያኖ ሮናልዶ የፔሌን ክብረወሰን መስበሩን ተከትሎ ከፔሌ የእንኳን ደስ አለህ መልእክት ደረሰው
በዘርፉ ያላሰበውን ስኬት ማስመዝገቡን ሮናልዶ ገልጿል
ሮናልዶ በኦፊሴላዊ ጨዋታዎች 770 ግብ በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብረወሰን ይዟል
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፣ በጣሊያን ሴሪ አ ትናንት ጁቬንትዩስ ከ ካግሊያሪ ጋር ባደረገው ጨዋታ 3 ጎል አስቆጥሯል፡፡ በዚህም ከዚህ ቀደም በብራዚላዊው ፔሌ ተይዞ የነበረውን በኦፊሴላዊ ጨዋታዎች የከፍተኛ ግብ አግቢነትን ክብረወሰን በእጁ አስገብቷል።
ፔሌ 767 ጎሎችን በማስቆር ክበረወሰኑን ይዞ የቆ ሲሆን ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በትናንትናው ጨዋታ ላይ ባስቆጠራቸው 3 ጎሎች ከበረወሰኑን በ3 ጎሎች በማሻሻል 770 አድርሷል፡፡
የ36 ዓመቱ ሮናልዶ 720 ሚሊዮን ተከታዮች ባሉት የኢንስታግራም ገጹ ላይ በዓለም ላይ ከፍተኛ ግብ አግቢ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ፣ ይህን ስኬት አስቦት እንደማያውቅም አስታውቋል።
የ80 ዓመቱ ብራዚላዊው ፔሌ በበኩሉ “በኢፊሴላዊ ጨዋታዎች የከፍተኛ ግብ አግቢ ክብረወሰኔን በመስበርህ እንኳን ደስ አለህ” ብሎታል።
ሮናልዶን እንደሚያደንቅ እና ጨዋታዎቹን መመልከት እንደሚያስደስተው የገለጸው ፔሌ፣ “አሁን የሚቆጨኝ ነገር አጠገብህ ሆኜ አንተን ማቀፍ አለመቻሌ ብቻ ነው” ብሏል።
በታሪክ 3 የዓለም ዋናጫዎችን ያነሳው ብቸኛው የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ፣ ኦፊሴላዊ ጨዋታዎችን ጨምሮ በእግር ኳስ ዘመኑ በአጠቃላይ 1,283 ጎሎችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።