ክርስቲያኖ ሮናልዶ ብዙ እግር ኳስ ቡድኖች የሌሏቸው ዋንጫዎች አሉት
እስካሁን ተሰልፎ በተጫወተባቸው 895 የክለብ ግጥሚያዎች በድምሩ 674 ጎሎችን ሲያስቆጥር 229 አመቻችቶ አቀብሏል
ወደ ዩናይትድ ለመመለስ እንደተስማማ የተነገረለት ሮናልዶ በጥቅሉ በክለብ ደረጃ የ32 ዋንጫዎች ባለቤት ነው
ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ለመመለስ እንደተስማማ የተነገረለት የ36 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የዓለም ኮኮብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ብዙ እግር ኳስ ቡድኖች የሌሏቸው ዋንጫዎች አሉት፡፡
ሮናልዶ በስፖርቲንግ ሊዝበን ለዋናው ቡድን አንድ ዓመት ብቻ ተጫውቶ 5 ጎሎችን አስቆጥሮ 6 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ (አሲስት) አቀብሏል፡፡
በ6 ዓመታት የእንግሊዝ ቆይታው ለማንችስተር ዩናይትድ በ292 ጨዋታዎች 118 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል፡፡
ክርስቲያኖ ወደ ስፔን በሪያል ማድሪድ በዋንጫ የታጀቡ አብረቅራቂ የስኬት ዓመታትን ነው ያሳለፈው፡፡
በ438 ጨዋታዎች 450 ጎሎችን በማስቆጠር “ግብ አዳኝነቱን አስመስክሯል”ም ነው የስፖርት ጋዜጠኞች እና ተንታኞች የሚሉት፡፡
ሮናልዶ እስካሁን ተሰልፎ በተጫወተባቸው 895 የክለብ ግጥሚያዎች በድምሩ 674 ጎሎችን ሲያስቆጥር 229 አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
በስም የሚጠቀሱ በርካታ እግር ኳስ ክለቦች ክርስቲያኖ ያለውን ያህል ዋንጫ የላቸውም፤ እሱ ያሸነፈውንም ያህል አላሸነፉም፡፡
በስፖርቲንግ እያለ በ17 ዓመቱ የፖርቹጋል ሱፐር ካፕን በማንሳት የጀመረው የዋንጫ አሸናፊነት ጉዞው በእንግሊዝ ሶስት የፕሪሚዬር ሊግ፣ የኤፍ ኤ ካፕ፣ ሁለት የሊግ ካፕ፣ ሁለት የኮሙኒቲ ሺልድ እና የዓለም የክለቦች ዋንጫን አንስቷል፡፡
በ2008 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቶም ነው ወደ ሪያል ማድሪድ ያቀናው፡፡
በማድሪድ ከ2016 እስከ 2018 በተከታታይ ያነሳቸውን ሶስት ዋንጫዎችን ጨምሮ በድምሩ አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አሸንፏል፡፡
ሁለት የላሊጋ፣ ሁለት የስፓኒሽ ካፕ፣ ሁለት የስፓኒሽ ሱፐር ካፕ፣ ሶስት የዓለም የክለቦች ዋንጫን እና ሶስት የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አንስቷል፡፡
የጣሊያን ሴሪ ኤን በተቀላቀለ የመጀመሪያው ዓመትም የሱፐር ካፕ እና የሴሪ ኤውን ዋንጫ ከጁቬንቱስ ጋር አንስቷል፡፡ ሁለቱንም ውድድሮች በድጋሚ አሸንፎ የጣሊያን ካፕን ማሸነፉም ይታወሳል፡፡
ሮናልዶ በጥቅሉ በክለብ ደረጃ የ32 ዋንጫዎች ባለቤት ነው፡፡
በ16 የተለያዩ ውድድሮች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሪከርድን ከመያዝም በላይ በ2009 በዩናይትድ ሳለ በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ፖርቶ ላይ ከረዥም ርቀት ባስቆጠራት የፑስካስ ሽልማትን ለማግኘት ችሏል፡፡
ክርስቲያኖ ልክ የክለብ እግር ኳስ ታሪኩን ያክል ባይሆንም በአምበልነት ከሚመራው የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር የ2016ቱን የአውሮፓ ዋንጫ ጨምሮ በርካታ ድሎችን አጣጥሟል፡፡
በ179 ጨዋታዎች 109 ጎሎችን በማስቆጠርም የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪም ነው፡፡
ገናናነቱን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ጭምር ያሳየው ሮናልዶ የፖርቹጋልን የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማትን 10 ጊዜ አሸንፏል፡፡