የስፖርቱ ዓለም በ2019 ምን አበይት ክስተቶችን አስተናገደ?
በአውሮፓውያኑ 2019 ዓለም በርካታ ስፖርታዊ ክዋኔዎችን አስተናግዳለች፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በዓመቱ የተከናወኑ አበይት ስፖርታዊ ክስተቶች እና ክዋኔዎች በዚህ ጽሁፍ ተዳስሰዋል፡፡
ኢትዮጵያና ስፖርት በ2019
ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች በሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተና ስኬት ያስመዘገቡበት፣ ፈተናዎችንም ያሳለፉበት ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡
አትሌቲክስ እና ኢትዮጵያ
በአትሌቲክሱ ዘርፍ በተለይም በረዥም ርቀት ስኬታማነት ስሟ ከፊት የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ፣ በተጠናቀቀው 2019 አትሌቶቿ በግልም ሆነ በቡድን ስራ በርካታ ድልና እውቅና አግኝተዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ውድድር፣ ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም ለስድስት ተከታታይ ቀናት በተካሔደው 48ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ ክብረወሰኖች ተሻሽለዋል፡፡ ቀጥሎም ከነሀሴ 13 እስከ 15 በተካሔደው በሞሮኮው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችም ሆነ በዶሀው የአለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ውጤት አስመዝግባለች፡፡
በተለይ በአለም ሻምፒዮናው በሌሊሳ ዴሲሳ እና ሙክታር እድሪስ ከተገኙት ወርቆች በላይ፣ ተስፋየታየባቸው ወጣት አትሌቶች በፈተና ለታጀበው የሀገሪቱ አትሌቲክስ ብርሀን ፈንጥቀዋል፡፡ ኬኒያውያን የባህል ስፖርት በሚሉት የ3ሺ መሰናክል 2ኛ የወጣው ለሜጫ ግርማ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር በአንዳንድ አትሌቶቿ የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት በ2019 ኢትዮጵያ በአሉታዊ ጎንም ስሟ ተነስቷል፡፡
ዓለማቀፍ ሽልማት
ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ መስክ ከውጤት ባሻገር 2019 ዓ.ም. ታላላቅ አትሌቶቿ እና የአትሌቲክሱ ፈርጦች እውቅና ያገኙበትም ነው፡፡
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የባርሴሎና ኦሎምፒክ ንግስቷን ደራርቱ ቱሉን ያኔ በውድድር አሁን በስፖርት አመራርነት እየተወጣች ላለችው በጎ ሚና የዓመቱ ምርጥ ሴት ብሎ ሸልሟታል፡፡ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ኃላፊው አቶ ቶሌ ጂሎ እና የቀድሞው አሰልጣኝ ወልደ መስቀል ኮስትሬ በአመቱ እውቅና የተሰጣቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ዓለም ሰዎች ናቸው፡፡ የአፍሪካ ስፖርት ፌደሬሽን ደግሞ በአትሌቲክስ እና የአመራር ብቃቱ ኃይሌ ገብረስላሴን ሸልሞታል፡፡
እግርኳስና ኢትዮጵያ
በርካታ ተመልካቾች ያሉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ከፍተኛ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ያሳየበት ዓመት ነበር 2019፡፡ አግርኳስን ፖለቲካዊ መልክ ያላበሱ ደጋፊዎች በቀሰቀሷቸው ጸቦች እና ግርግሮች በዓመቱ በሰው አካል እና ንብረት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል፡፡
በተለይ ችግሩ ከአዲስ አበባ ውጭ በክልሎች ጎልቶ ታይቷል፡፡ስፖርታዊ ጸብና ቁርሾ ዉስጥ የገቡ ክልሎች፣ ክለቦቻቸው በገለልተኛ ሜዳ ለመጫወት ተገደዋል፡፡ ይሄም ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ለመቀነስ አስችሏል፡፡
የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሉ እያየለ መሄድ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በተደጋጋሚ የሚከለስ ወጥ ያልሆነ ህግ እንዲያወጣ አስገድዶታል፡፡
የተያዘው ዓዲሱ የውድድር ዓመት አጀማመሩ በመከባበር እና በፍቅር መሆኑ ያዝልቀው የሚያስብል ነው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት እንከኖች በተቃራኒ ኢትዮጵያዊቷ አጥቂ ሎዛ አበራ በማልታ ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆና የሀገሯን ስም እየስጠራች ነው፡፡ በብዛት በደካማ አቋሙ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በእግርኳሱ ዘርፍ ገናና ስም ያላትን ኮትዲቮርን ከ52 ዓመታት በኋላ ያሸነፈውም በዚሁ በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ ዓመት ነው፡፡ፕሪሚየር ሊጉ ደግሞ በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ስፖርት በዓለም እይታ
በተጠናቀቀው 2019 በመላው ዓለም በርካታ ስፖርታዊ ሁነቶች ቢከናወኑም የኢትዮጵያውያንን ቀልብ የሳቡት ጥቂቶች ናቸው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ
ግብጽ ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ አልጄሪያ ስታሸንፍ ድሉ በወቅቱ፣ ለጊዜውም ቢሆን፣ በሀገሪቱ የተደቀነውን የፖለቲካ ቀውስ ለማርገብ ረድቷል፡፡አልጄሪያ በባግዳድ ቦንድጃህ የ2ኛ ደቂቃ ብቸኛ ጎል በፍጻሜው ሴኔጋልን በመርታት ሁለተኛ ዋንጫዋን አሳክታለች፡፡
የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር መሪ የነበሩት ቡተፍሊካ አገዛዝ በህዝቡ ተጠልቶ የነገሰው ውጥረት ባየለበት ወቅት የአፍሪካ ዋንጫ ድል መምጣቱ ሀገሪቱ እንደጎረቤቶቿ ሊቢያና ቱዚያ እንዳትሆን ታድጓታል፡፡
የሴቶች ዓለም ዋንጫ
በአመቱ በተካሄደው የሴቶች ዓለም ዋንጫ ልዕለ ሀያሏ ሀገር አሜሪካ የአውሮፓ ሻምፒዮንዋን ኔዘርላንድን 2 ለ 0 በማሸነፍ ባለድል ሆናለች፡፡ አሜሪካ የ1991፣ የ1999 እና የ2015 ድሏን ጨምሮ ዋንጫውን ለ4ኛ ጊዜ በማንሳት ክብረወሰን ይዛለች፡፡ ከድሉ ጋር ተያይዞ የተከሰተው አስገራሚ ክስተት የቡድኑ አምበል እና የውድድሩ ኮከብ ሜጋን ራፒኖ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቤተመንግስት የተደረገላትን ግብዣ አልቀበልም ማለቷ ነው፡፡ ራፒኖ በተለይ ለሴቶች ክብር የለውም ከምትለው ትራምፕ ጋር ባላት ልዩኘት ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተደጋጋሚ የቃላት ልውውጥም አድርጋለች፡፡
ሌሎች ውድድሮች
በዓመቱ በተካሄዱ ሌሎች ውድድሮች ብራዚል የኮፓ አሜሪካን ዋንጫ፣ ኳታር የኢሲያን ዋንጫ፣ ፖርቹጋል የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ሀገራት ሊግን ሲያሸንፉ፤ በአመቱ እንግሊዝ በገነነችበት የአውሮፓ የእግርኳስ መድረክ ውድድሮች ሊቨርፑል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ቼልሲ ደግሞ የዩሮፓ ሊግን በበላይነት አጠናቀዋል፡፡
የሩሲያ እገዳ
ዓመቱ በመጠናቀቂያው ወር ለ2018 የዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ሩሲያ አስከፊ ትዝታን ጥሎም አልፏል፡፡ የመንግስት እጅ አለበት በተባለው የሀገሪቱ ስፖርተኞች የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት ክስ የቶኪዮ ኦሎምፒክ እና የኳታር ዓለምዋንጫን ጨምሮ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ከማኝኛውም ስፖርታዊ ውድድር እንድትታገድ ዓለማቀፉ የጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ-ዋዳ ወስኗል፡፡
ውሳኔው ያልተዋጠላቸው የሀገሪቱ መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጉዳዩ ከስፖርት ይልቅ ፖለቲካዊ ተልእኮን ያዘለ ነው በማለት ውሳኔውን አጣጥለውታል፡፡