“ደብዳቤው ኮሚሽኑ ማስተላለፍ የፈለገውን ትክክለኛ መልዕክት አላስተላለፈም” የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ለአል ዐይን
ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ የተጻፈው አወዛጋቢው የስፖርት ኮሚሽን ደብዳቤ ተሻረ
የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የጻፈው ደብዳቤ በህዝባዊ አካል ማለትም በፌዴሬሽኖች ላይ ተፈጻሚነት እንደሌለው አስታወቀ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ካለው የትግራይ ምርጫ ጋር ተያይዞ የፌደራል መንግስት ተቋማት ከትግራይ ክልል ም/ቤት እና ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል ወይም ካቢኔ ጋር ምንም አይነት ህጋዊ ግንኙነት ማድረግ እንደማይችሉ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ም/ቤት እና ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል ወይም ካቢኔ አሊያም በክልል ደረጃ ካሉ አስፈፃሚ አካለት ጋር እንደ ህጋዊ አካላት በመቁጠር ደብዳቤ መፃፃፍ፣ ዶክመንት መላላክ፣ በፌዴራል ደረጃ በሚካሄዱ መድረኮች ላይ ማሳተፍ እንደማይቻል ተወስኗል፡፡
የፌደራል ስፖርት ኮሚሽንም ይህን ውሳኔ እንዲያስፈፅሙ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ እንዲሁም ፓራሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ለ20 ፌዴሬሽኖች እና 8 ማህበራት በቀን 9/2/2013 ዓ.ም. ደብዳቤ ልኳል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን የታዘዘው በመንግስታዊ አደረጃጀቱ በክልል ም/ቤት እና ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል ወይም ካቢኔ ጋር እንጂ ሕዝባዊ አደረጃጀቶችን የማይመለከት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ደብዳቤው ከፍተኛ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ይሁንና ደብዳቤው የመረጃ ክፍተት ያለበት መሆኑን በመጥቀስ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ትናንት ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የመጀመሪያው ደብዳቤ መሻሩን ገልጿል፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አል ዐይን አማርኛ በስልክ ያናገራቸው የስፖርት ኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ በ 9/2/2013 ዓ.ም የተጻፈው ደብዳቤ ኮሚሽኑ ማስተላለፍ የፈለገው ትክክለኛ መልዕክት ያልተላለፈበት እና የመረጃ ክፍተት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በስሩ ለሚገኙት ኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፣ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ፣ ለ20 ፌዴሬሽኖች እና 8 ማህበራት ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልልን በሚመለከት ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲያውቁ ማድረግ እንደሆነ ነው አቶ ናስር የገለጹት፡፡ በዚህም ለስፖርታዊ ተግባራት ከትግራይ ክልል የፖለቲካ አመራር ጋር የሚኖራቸውን የትብብር እና መሰል ግንኙነቶች በምን መልኩ ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ለማሳሰብ እንደሆነ አቶ ናስር አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚገኙ መሰል የስፖርት ሕዝባዊ አደረጃጀቶች ጋር እንዳይገናኙ የማድረግ ተልዕኮም ፍላጎትም የለውም ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ይሁንና አቶ ናስር ደብዳቤውን በጻፈው ግለሰብ የተፈጠረ የአገላለጽ ስህተት ነው ያሉት በደብዳቤው የሰፈረው ጽሁፍ በተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች እና ማህበራት ዘንድም ጭምር ከፍተኛ ብዥታ የፈጠረ እና ወደ ኮሚሽኑ ብዙ ጥያቄ እንዲመጣ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ኮሚሽኖች እና ማህበራት በተሳሳተ መንገድ ወደ ትግበራ ለመግባት ተዘጋጅተው እንደነበርም ነው አቶ ናስር ለአል ዐይን የገለጹት፡፡
ይሁን እንጂ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልልን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ በአባሪ የያዘ ደብዳቤ መላኩን ያስታወሰው ኮሚሽኑ፣ የተጻፈውም ደብዳቤ የመረጃ ክፍተት ያለው በመሆኑ የተሻረ መሆኑን የሚያሳውቅ በፌዴራል ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር ዱቤ ጅሎ የተፈረመ ደብዳቤ በድጋሚ አውጥቷል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ኮሚሽኑም ሆነ ተጠሪ ተቋማት ከትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ካቢኔ ወይም በክልል ደረጃ ካሉ ስራ አስፈፃሚ አካላት ማነኛውንም ግንኙነት ማድረግ አይችሉም የሚለው ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ብሏል ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፡፡
ነገር ግን የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ከክልል የስፖርት ፌዴሬሽኖች ፣ ክለቦች እና ቡድኖች ጋር የሚያደርጉት ማነኛውም ግንኙነት ስልጠናዎች ውድድሮች እና አጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቋል፡፡