እስራኤል ከአሁን በኋላ የሚሰነዘሩባትን የሚሳዔልና ሌሎችንም ጥቃቶች ለመመከት ሁለት ዶላር ብቻ እንደምታወጣ ገለጸች
'አይረን ቢም' ጠላት የሚተኩሰውን ብቻም ሳይሆን ኢኮኖሚውንም ይመታል ተብሎለታል
እስራኤል 'ጨዋታ ቀያሪ' ያለችውን የጨረራ ቴክኖሎጂ በቀጣዩ ዓመት ተግባር ላይ እንደምታውል አስታውቃለች
እስራኤል ከአሁን በኋላ የሚሰነዘሩባትን የሞርታርና ሌሎችንም ጥቃቶች ለመመከት ሁለት ዶላር ብቻ እንደሚጠይቃት ገለጸች፡፡
እስራኤል 'ጨዋታ ቀያሪ' ያለችውንና በጨረራ ቴክኖሎጂ (ሌዘር) የሚታገዘውን 'አይረን ቢም' የተሰኘ ዘመናዊ የመከላከያ ቴክኖሎጂ በቀጣዩ ዓመት ተግባር ላይ እንደምታውል አስታውቃለች፡፡
የጨረር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሞርታር፣ ሮኬትና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) ለይቶ እንደሚመታ የተነገረለትን ዘመናዊ ጦር መሳሪያ የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት 'ጨዋታ ቀያሪ' ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ቤኔት 'ጨዋታ ቀያሪ' ስላሉት የመከላከያ ቴክኖሎጂ ሲያወሩ በ 'አይረን ቢም' ጠላት የሚተኩሰውን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም እንመታለን ብለዋል፡፡
እስራኤል 'አይረን ዱም'ን መሰል የመከላከያ ስርዓት በመጠቀም የሚሰነዘሩባትን የሚሳዔልና ሌሎችንም ጥቃቶች አየር ላይ ስታመክንና ከተሞቿን ከውድመት ስትታደግ ነበር፡፡
ሆኖም 'አይረን ዱም' እና ሌሎችም የመከላከያ መንገዶች ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በመቶ ሺዎችና በሚሊየን ዶላሮች የሚጠጋ ወጪን ማውጣትም ግድ ነበረ፡፡
ነገር ግን አሁን ይህ ቀርቷል ተብሏል፡፡ 'አይረን ቢም' የሚጠይቀው ተተኳሾችን በሚያመክንበት ወቅት የሚጠቀመውን የኤሌክትሪክ ፍጆታ መሸፈን ብቻ ነው፡፡ ይህም ሁለት ዶላርን የሚጠይቅ ነው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት ገለጻ፡፡