አፍሪካ በዓለም ዋንጫው አዲስ ታሪክ እንድታስመዘግብ ምክንያት የሆነችው ሞሮኮ ተጨማሪ ታሪክ እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል
በዓለም ዋንጫው ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ሞሮኮ ከክሮሺያ ይጫወታሉ።
በኳታር አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው የ2022 የዓለም ዋንጫው ነገ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የውድድሩ መርሀግብር ያስረዳል።
አርጀንቲና እና ፈረንሳይ የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ ሲሆኑ አፍሪካዊቷ ሞሮኮ እና ክሮሺያ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ለማጠናቀቅ ይጫወታሉ።
አፍሪካ በዓለም ዋንጫው አዲስ ታሪክ እንድታስመዘግብ ምክንያት የሆነው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ተጨማሪ ታሪክ እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል።
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዋሊድ ሪግራጉይ እንዳሉት በፍጻሜው ውድድር ላይ መሳተፍ እንፈልግ ነበር ነገር ግን በፈረንሳይ ተሸንፈናል ብለዋል።
ይሁንና ለደረጃ ጨዋታ መጫወታችን ሌላ ታሪክ እና እድል ሊሰጠን ስለሚችል ከክሮሺያ ጋር ለምናደርገው ጨዋታ ትኩረት እንሰጣለን ብለዋል።
ለፍጻሜ ለማለፍ በተደረገው ጨዋታ ላይ በአርጀንቲና ሽንፈትን ያስተናገዱት ክሮሺያዎች ሞሮኮን ለማሸነፍ እንደሚጫወቱ አሰልጣኙ ተናግረዋል።
ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሚደረገው የደረጃ ጨዋታ አሸናፊው ብሔራዊ ቡድን ሶስተኛ ተሸናፊው ደግሞ አራተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቅ ይሆናል።
ክሮሺያ በሩሲያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የ2018 ዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሰው በፈረንሳይ መሸነፋቸው ይታወሳል።
የክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሉካ ሞድሪች የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ እንደሚሆን ተገልጿል።
ከዓለም ዋንጫው የተሰናበቱ ብሄራዊ ቡድኖች ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ራሳቸውን እያገለሉ ይገኛሉ።
ስፔናዊ ሰርጂዮ ቡስኬት፣ የቤልጂየሙ ኤደን ሀዛርድ፣ ብራዚሊያዊው ሲልቫ እና ሌሎችም ያገለሉ ተጫዋቾች ናቸው።
ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ውስጥ ደግሞ የስፔን፣ ቤልጂየም፣ብራዚል፣ ፖርቹጋል፣ ኢራን፣ ሜክሲኮ፣ ፖላንድ፣ ኔዘርላንድ እና ሌሎችም ከአሰልጣኝነታቸው ተነስተዋል።