በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ሲጫወቱ የክለቦች አይን ያረፈባቸው ተጫዋቾች
በአለም ዋንጫው ያልተጠበቁ ጎል አስቆጣሪዎችና ግብ ጠባቂዎች የክለቦችን መልማዮች ቀልብ መሳባቸው እየተነገረ ነው
የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ተስፈኛው ኤዜዲን ኡናሂ፣ የሳኡዲው ሳኡድ አብዱልሃሚድ እና የክሮሽያው ዶሞኒች ሊቫኮቪች ከዋናዋናዎቹ መካከል ናቸው
ፔሌ በ1958 የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ጨዋታ ሲያደርግ እድሜው 17 አመት ነበር።
ማይክል ኦውንን የ1998ቱ፣ ሮናልዲንሆን የ2002ቱ፣ ማሪዮ ጎትዘን የ2014ቱ የአለም ዋንጫ ነው ለአለም ያስተዋወቃቸው።
የኳታሩ የአለም ዋንጫ እንደ ክሊያን ምባፔ፣ ጋቪ፣ፔድሪ፣ ሪቻልሰን፣ ጎንሳሎ ራሞስ ያሉ የነገ ከዋክብትን አሳይቶናል።
በዶሃ ደምቀው ከታዩት ተስፈኞችና የዝውውር ቀልብ የሳቡ ተጫዋቾች መካከል ሰባቱን እንመልከት፥
ኤዜዲን ኡናሂ - ሞሮኮ እና ኦንዤ
ስፔን በሞሮኮ በመለያ ምት ተሸንፋ ከሩብ ፍጻሜው ውጭ ስትሆን አሰልጣኝ ልዊስ ኤነሪኬ ነጥሎ ያወደሰው የሞሮኮ ተጫዋች ኤዜዲን ኡናሂን ነው። ኡናሂ በፈረንሳይ ሊግ በደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ለሚገኘው ኦንዤ መጫወት ከጀመረ ገና 18 ወራት ብቻ ተቆጥረዋል። ለሀገሩም ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የተሰለፈው። ይሁን እንጂ ይራስ መተማመኑና የቡድን ጨዋታ አዋቂነቱ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ነው ያስመሰሉት። ሃገሩን እስከ ግማሽ ፍጻሜ ያደረሰው የ22 አመቱ ኡናሂ፥ በኦንዤ እስከ 2025 የሚያቆይ ውል ቢኖረውም በቀጣዩ የዝውውር መስኮት የተሻለ ክለብን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።
ሳኡድ አብዱልሃሚድ - ሳኡዲ አርቢያ እና አል ሂላል
ሳኡዲ አርጀንቲናን 2 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታ የሜሲ እና የቡድን አጋሮቹን የማጥቃት ሙከራ ሁሉ ከንቱ ያደረገው አብዱልሃሚድ ነበር። የ23 አመቱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ፍጥነቱ፣ ኳስ የማስጣል ብቃቱና ከአማካዮች ጋር መናበቡ በበርካታ ክለቦች እየተፈለገ ነው። ለሳኡዲው አል ሂላል የሚጫወተው ሳኡድ አብዱልሃሚድ፥ በሲቪያ፣ ኤሲ ሚላን እና ጁቬንቱስ መልማዮች አይን ውስጥ ገብቷል። ሳኡዲን በአምበልነት እየመራ በኳታር የተገኘው አብዱልሃሚድ በአለም ዋንጫው ራሱን ገልጦ አሳይቷል።
ያሲን ቦኖ - ሞሮኮ እና ሲቪያ
ሞሮኮ ትልልቆቹን ክለቦች እየጣለች ለግማሽ ፍጻሜው ስትደርስ የግብ ጠባቂው ቦኖ ሚና ድንቅ ነበር።
ሲቪያ የ2020 የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ኢንተር ሚላንን አሸንፎ ሲያነሳ ብቃቱ ጎልቶ መታየት የጀመረው ግብ ጠባቂው በኳታር ነግሶ ስንብቷል። ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ከስፔን ጋር በተደረገው ጨዋታ ሁለት መለያ ምቶችን አድኗል።
በካናዳ የተወለደው የ31 አመት ግብ ጠባቂ ከፖርቹጋል ጋር ሲፋለሙም ሀገሩን ታድጓል። ብዙ ቋንቋ ተናጋሪው በዶሃ ያሳየው ብቃት የመልማዮችን ትኩረት እንዲይዝ አድርጎታል ተብሏል።
ሪትሱ ዶዋን - ጃፓን እና ፍሬቡርግ
ጃፓን በኳታሩ የአለም ዋንጫ የአራት ጊዜ ሻምፒዮኗን ጀርመን እና የ2010 የዋንጫው ባለቤትን ስፔን ያሸነፈችባቸው ጨዋታዎች በሩቅ ምስራቋ ሀገር የእግር ኳስ ታሪክ መቼም አይዘነጉም። ሪትሱ ዶዋንም የዚሁ ታሪክ ጉልህ ተጋሪ ነው። በሁለቱም ሀገራት ላይ ተቀይሮ እንደገባ ጎል ያስቆጠረው የ24 አመት ተጫዋች የጃፓኑ ሜሲ ተብሎ እስከመጠራት ደርሷል።
ኤሳ ላይዳውኒ - ቱኒዚያ እና ፌነርባቼ
ቱኒዚያ በምድብ ጨዋታዎች ከዴንማርክ እና አውስትራሊያ ጋር ስትጫወት በወኔ ሞልቶ የተለየ ብቃቱን ያሳየው ላይዳውኒ ነው። ፈረንሳይን ባሸነፉበት ጨዋታም የፌነርባቼው አማካይ ወሳኝ ድርሻ ነበረው። በፈረንሳይ የተወለደው የ26 አመት ኮከብ ሀገሩ ቱኒዚያ ከምድቧ ሳታልፍ ብትቀርም በኳታር የበርካታ ክለቦች ትኩርትን ስቧል ተብሏል።
ዶሞኒች ሊቫኮቪች - ክሮሽያ እና ዳይናሞ ዛግሬብ
በኳታር ከታዩ ግብ ጠባቂዎች ከፊት ተርታ የሚሰለፈው ሊቫኮቪች ጃፓን እና ብራዚልን ጉድ ስርቷል ፤ የመለያ ምቶችን በማዳን ሀገሩን እስከ ግማሽ ፍጻሜው በማድረስ። የ27 አመቱ ግብ ጠባቂ በኳታር ባሳየው ብቃት ባየር ሙኒክን ጨምሮ በርካታ ክለቦች የፊርማ ጥያቄ እያቀረቡለት መሆኑ ተሰምቷል።
ሃሪ ሱታር - አውስትራሊያ እና ስቶክ
አውስትራሊያ በአለም ዋንጫው ቱኒዚያን አሸንፋ ከ12 አመት በኋላ ወደ ድል ስትመልስም ሆነ ዴንማርክን በረታችበት የምድብ ጨዋታ ያልተጠበቀው ሱታር ትልቁን ሚና ተጫውቷል።
ለእንግሊዙ ስቶክ የሚጫወተው ሱታር በዚህ አመት በሻምፒዮንስሺፑ በአንድ ብቻ ጨዋታ ነበር የተሰለፈው። በዶሃ ያሳየው ብቃት ግን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የተሻለ እድል ሰጥተው እንዲያሰፈርሙት የሚያደርግ ነው።