አንድ የአዞ ቆዳ ከ350-400 ዶላር ለቻይና፣ ጀርመን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት በመሸጥ ላይ መሆኑን እርባታ ማእከሉ ገልጿል
ከአዲስ አበባ 443 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አርባ ምንጭ ከተማ የጎብኚዎችን ትኩረት የሚስቡ በርካታ መዳረሻዎች አሏት፡፡
በ1976 ዓ.ም በግብርና ሚኒስቴር ተቋቁሞ በ1982 ዓ.ም ስራ የጀመረው የአዞ ማራቢያ ማእከሉ ወይም ራንች ዋነኛው የአርባምንጭ ገጽታ ነው፡፡
በዚህ ማዕከል በአስጎብኚነት እየሰራ የሚገኘው አቶ አስደሳች ዳንኤል ለአል ዓይን እንዳለው ማዕከሉ ከ38 ዓመት በፊት የተቋቋመው የአዞ ዝርያ እንዳይጠፋ በሚል ነበር፡፡
በወቅቱ የአሳ አስጋሪዎች እና ህገወጥ አዞ አዳኞች እንስሳውን በስፋት በመግደላቸው ዝርያው ወደመቀነስ መጥቶ ነበር የሚሉት አቶ አስደሳች ማዕከሉ መቋቋሙን ተከትሎ የአዞ ዝርያ እንዳይጠፋ ከማድረግ ባለፈ ማዕከሉ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ለአብነትም የሀገር ውስጥ እና የውጪ እንስሳት ተመራማሪዎች ጭምር ስለ አዞ ተጨማሪ ጥናቶችን የሚያደርጉበት ማዕከል መሆኑንም አስጎብኚው ነግረውናል፡፡
በደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስር የሚተዳደረው ይህ ማዕከል በቀን በትንሹ 250 ሰዎች ይጎበኙታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዚህ ማዕከል ውስጥ ከ4 ዓመት እስከ 7 ዓመት እድሜ ያላቸው 2 ሺህ 700 አዞዎች እንዳሉ የተናገሩት አስጎብኚው ቆዳቸውን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ላይ ነውም ብለዋል፡፡
አንድ የአዞ ቆዳ ከ350-400 ዶላር በመሸጥ ላይ ሲሆን ቻይና፣ ጀርመን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ደግሞ ቆዳውን የሚገዙ ሀገራት ናቸው፡፡
አንድ እንስት አዞ በአባያ እና ጫሞ ሀይቅ ዳርቻ ስፍራዎች ላይ በየዓመቱ ታህሳስ ወር ላይ እንቁላል የምትጥል ሲሆን እንቁላሎቹ ከ90 ቀናት በኋላ ይፈለፈላሉ፡፡
የአዞ ጫጩቶቹን የማዕከሉ ሰራተኞች ከሁለቱ ሀይቆች ዳርቻ ይዘው ወደ ማዕከሉ በማምጣት ጫጩቶቹ እንደየእድሜያቸው በተዘጋጀላቸው ስፍራዎች እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡
አዞዎቹ እድሜያቸው 4 ዓመት እና በላይ ሲሆናቸው ድምጽ በሌለው መሳሪያ ከተገደሉ በኋላ በቆዳ ገፋፊ ባለሙያዎች መሰረት ቆዳቸው ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ሌሎች የውጭ ሀገራት ይሸጣል፡፡
የአዞ ቆዳ ለጫማ፣ ቦርሳ፣ ጃኬት፣ ቀበቶ፣ ጓንት እና ሌሎች ውድ የቆዳ ምርት ቁሳቁሶችን ለማምረት ይውላል፡፡አንድ በባለሙያ የተገደለ አዞ ቆዳው ከተገፈፈ በኋላ ስጋው መልሶ ለሌሎች አዞዎች ለምግብነት እንደሚውልም አስጎብኚው ገልጸዋል፡፡
አዞ ምላስ የሌለው እንስሳ በመሆኑ የተሰጣቸውን ሳያደቁ ስለሚመገቡ ቶሎ አይርባቸውም የሚሉት አቶ አስደሳች በሳምንት ሁለት ጊዜ ስጋ ብቻ እንዲመገቡ ይደረጋልም ብለዋል፡፡አንድ አዞ ከ250-400 ግራም ስጋ በአንዴ የሚመገቡ ሲሆን የሚንከባከቧቸውን ሰዎች በጠረን መመለየትም ይችላሉ ሲሉ አቶ አስደሳች ይናገራሉ፡፡