የግብርና ሚኒስቴር 110 ሺህ ውሾችን ሊከትብ መሆኑን ገለጸ
አገር አቀፍ ውሾችን የመከተብ መርሃግብር ዛሬ በአርባ ምንጭ ተጀምሯል
ክትባቱ ግብርና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትብብር የሚሰጥ ነው
የግብርና ሚኒስቴር 110 ሺህ ውሾችን ሊከትብ መሆኑን ገለጸ።
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው በተያዘው 2014 በጀት ዓመት የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል 110 ሺህ ውሾችን እከትባለሁ ብሏል።
በዚህ መሰረት የዘንድሮ አለም አቀፍ የዉሻ እብደት በሽታ ቀን ምክንያት በማድረግ የክትባት ዘመቻውን የግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ በይፋ መጀመሩን ገልጿል።
የክትባት ዘመቸውን በኦሮሚያ እና በሲዳማ ክልሎች ቀድሞ የተጀመረ ሲሆን፤ በሌሎችም ክልሎች በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት እንደሚቀጥል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክቶሬት በዘመቻው ላይ ተገኝተው እንደገለፁት በየዓመቱ ክትባቱን ለውሾች በመስጠት ለበሽታዉ እንዳይጋለጡ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰዎች በውሻ በሚነከሱበት ወቅት ለመከላከል የሚሰጥ ክትባት እንዳለ ገልፀው ክትባቱም በሀገራችን በመመረት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የበሽታው አስከፊነት እስከ ሞት የሚያደርስ እንደመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ውሾችን የማስከተብ አማራጭን መጠቀም እንደሚገባ እንደሚያሳስብ በዘመቻው ላይ የተሳተፉት የግብርና ሚኒስቴር የቬተርናሪ ፐብሊክ ሄልዝ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጌታቸው ገልፀዋል።