ለራሰ በራዎች ተስፋ የሰነቀ በ“3ዲ” ቴክኖሎጂ የተሰራ ጸጉር
የአሜሪካ ተመራማሪዎች በሚሊየን ለሚቆጥሩ ራሰ በራዎች መፍትሄ የሚሆን ምርምራቸውን ይፋ አድርገዋል
ተመራማሪዎቹ በላብራቶሪ ባደገ የሰው ልጅ የቆዳ ህብረ ህዋስ ላይ በ”3ዲ” ቴክኖሎጂ ጸጉር አብቅለዋል
በአለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የራሰ በራነት ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት መቃረባቸውን የአሜሪካ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።
በኒውዮርክ የሚገኘው የሬንሳሌር ፖሊቴክኒክ ተቋም በሳይንስ ጆርናል ላይ ያሳተመው የጥናት ውጤት ለሚሊየን ራሰ በራዎች ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ በላብራቶሪ ባደገ የሰው ልጅ የቆዳ ህብረ ህዋስ ላይ በ”3ዲ” ቴክኖሎጂ ጸጉር ማብቀል መቻላቸው ነው የተገለጸው።
የጥናቱ መሪ ዶክተር ፓንካጅ ካራንዴ እንደሚሉት ጥናቱ በ”3ዲ” ቴክኖሎጂ የጸጉር አበቃቀል ስርአትን መቀየር እንደሚቻል ያሳየ ነው።
የሰው ልጅ ቆዳ ህብረ- ህዋስ የጸጉር አበቃቀል ስርአቱን በ”3ዲ” ቴክኖሎጂ ማስተካከል ከተቻለ አዲስ ጸጉር ማብቀል እንደሚቻል አረጋግጠናልም ነው ያሉት።
ምርምሩ የቆዳ ህብረ - ህዋስ (ቲሹ) በሶስት አቅጣጫ (3ዲ) እንዲዳብር ከተለማማመደ የጸጉር ዘለላዎችን በፍጥነት ማሳደግ የመቻል አቅሙ እንደሚያድግ ማሳየቱንም ዶክተር ፓንካጅ ካራንዴ ተናግረዋል።
የጸጉር ዘንጎች እርጥበትን የመያዝ፣ የሰውነት ቆዳን የመቆጣጠር እና ቆዳን ከአደጋ የመጠበቅ አቅም አላቸው።
ስለሆነም በ”3ዲ” ቴክኖሎጂ የእነዚህን የጸጉር ዘንጎች እድገት ማፋጠን መቻልና ተገቢውን ንጥረነገር በስፋት የሚያገኙበትን አቅጣጫ ማስፋት ራሰ በራነትን ለማስወገድ መፍትሄ ሆኖ ቀርቧል።
ራሰ በራነት ከእድሜ መግፋት ባሻገር በዘር፣ በሆርሞን ለውጥ ወይንም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በወጣትነት ሊከሰት ይችላል።