ግጭቱ በኑባ እና ቤኒ ዓምር ጎሳዎች መካከል የተቀሰቀሰ ሲሆን 80 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል
ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ከሰላ ከተማ የጎሳ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ሱዳን ሰዓት እላፊ ጣለች፡፡
ሰዓት እላፊው በኑባ እና ቤኒ ዓምር ጎሳዎች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ትናንት ረቡዕ ምሽት ጀምሮ የተጣለ ሲሆን ለ24 ሰዓታት ይቆያል ተብሏል፡፡
ሌላ አዲስ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ሰዓት እላፊው እንዲከበርም የከተማዋ ባለስልጣናት አሳስበዋል፡፡
ደም አፋሳሽ ነበር የተባለለትን ግጭት የሃገሪቱ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች ገብተው እስኪያስቆሙት ድረስ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ጉዳቶች መድረሳቸው ተገልጿል፡፡
ከአሁን በፊት የምስራቅ ሱዳን አካል በሆኑት በከሰላ፣ በቀይ ባህር (ፖርት ሱዳን) እና በገዳሪፍ ክልሎች ተቀስቅሶ በነበረ ተመሳሳይ ግጭት 80 ሰዎች በሁለቱም ጎሳዎች በኩል መሞታቸው ተነግሯል፡፡
በደቡብ ሱዳን ጁባ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በሃገሪቱ መንግስት እና በአማጽያን መካከል የነበረውን ግጭት በማርገብ አንጻራዊ ሰላምን ለሱዳን ለማጎናጸፍ ቢችልም የጎሳ ግጭቶች ግን አሁንም ቀጥለዋል፡፡
በቅርቡ በምዕራባዊ ዳርፉር በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት የ200 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
በጄ/ል አል ቡርሃን የሚመራውና ሁኔታዎችን የገመገመው የሱዳን የሽግግር መንግስት ግጭቶችን ለመቆጣጠር የጦር ኃይል አባላቱን በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እንደሚያሰማራም ትናንት ገልጿል፡፡
ከሰላ ሱዳንን በዋናነት በተሰነይ በኩል ከኤርትራ፤ በሁመራ በኩል ደግሞ ከኢትዮጵያያጎራብታል፡፡