የሱዳን የፖለቲካ ተዋናዮች በግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ሁሉን አቀፍ ውይይት ሊያደርጉ ነው ተባለ
በሱዳን ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ በጊዜ ካልተፈታ በሀገሪቱ የባሰ አለመረጋጋት እንዳይፈጠር ተሰግቷል
ሱዳን በፈረንጆቹ ከጥቅምት 25 2021 በኋላ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃለች
በሱዳን የፖለቲካ ተዋናዮች መካከል ሁሉን አቀፍ ውይይት ከግንቦት 10 እስከ ግንቦት 12 እንደሚካሄድ የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ሞሃመድ ኤል ሀሰን ኦልድ ሌባት አስታወቁ።
ልዩ መልዕክተኛው፤ ውይይቱ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሃይሎች ፍትሃዊ እና ግልጽ ሀገራዊ ውይይት እንዲያደርጉ ከማስቻል በዘለለ ሁሉንም ተዋናዮች ወደ ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ ሂደት የሚያደርጉትን ሽግግር የተቃና ለመድረግ በሚያስችል ስምምነት ላይ የሚደርሱበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሱዳን የተባበሩት መንግስታት የተቀናጀ የሽግግር እርዳታ ተልእኮ ኃላፊ ቮልከር ፔርቴስ በበኩላቸው፤ በሱዳን ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ እስካልተፈታ ድረስ በሀገሪቱ የባሰ አለመረጋጋት እንዳይፈጠር ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ውይይቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ያደረጉትን ጥረት ተከተሎ የሚካሄድ መሆኑም ነው የተገለጸው።
የሱዳን ጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌተና ሄነራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን እንደፈረንጆቹ ጥቅምት 25 ቀን 2021የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሉዓላዊ ምክር ቤቱን እና መንግስትን ካፈረሱ በኋላ፤ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም እና ሌሎች ከተሞች ወደ ሲቪል አገዛዝ እንዲመለሱ የሚጠይቁ ተቃውሞዎች ቢደመጡም፤ በቅረቡ ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት ሲባል የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚለቅ የጦሩ መሪና የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ሃገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ስምምነት ላይ የሚደርሱና የሚግባቡ ከሆነ ጦሩ ስልጣን ለመልቀቅና ለሲቪሊያን ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል ፕሬዝዳንቱ።