የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ገንዘብ አጀንዳ አለመሆኑን ደቡብ አፍሪካ ተናገረች
የአሜሪካ አጋር ያልሆኑ ሀገራት ከዶላር ውጭ አማራጮ የገንዘብ ስርዓት እያማተሩ ነው
ለጋራ ገንዘብ ምስረታ የባንክ ህብረትና የማክሮ ኢኮኖሚ ውህደት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል
በሚቀጥለው ወር በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ መገበያያ ገንዘብ አጀንዳ አይሆንም ተብሏል።
ነገር ግን ብራዚል፣ሩሲያ፣ህንድ፣ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ከአሜሪካ ዶላር የመውጣት መንገዳቸውን እንደሚቀጥሉ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የብሪክስ ዲፕሎማት አስታውቀዋል።
በደቡብ አፍሪካ የብሪክስ አምባሳደር አኒል ሱክላል "ስለ ብሪክስ ገንዘብ በጭራሽ አልተወራም። በአጀንዳው ላይም የለም" ብለዋል።
"የተናገርነው እና የበለጠ እየተጠናከርን የምንሄድበት ጉዳይ በሀገር ውስጥ ምንዛሬዎች መገበያየት እና በሀገር ውስጥ ምንዛሪዎች ክፍያ መፈጸም ነው" ሲሉም አክለዋል።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የጋራ መገበያያ ገንዘብን ሀሳብ በመወትወት፤ ህብረቱ የምዕራባውያንን የፋይናንስ የበላይነት መቃወም አለበት ካሉ የብሪክስ መሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ይህን ያሉት ባለፈው ዓመት የዩክሬንን ጦርነት መጀመርን ተከትሎ ሩሲያ ላይ ማዕቀብ ሲጣል ነው።
ይህም ሀገራት ከዶላር ውጭ አማራጮችን እንዲፈልጉ ገፋፍቷቸዋል ተብሏል።
ሆኖም የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ "ምንዛሬዎች ለረጅም ጊዜም ሀገራዊ ጉዳይ እንደሚሆኑ" ተናግረዋል።
የደቡብ አፍሪካ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ለጋራ ገንዘብ፤ የባንክ ህብረት፣ የፊስካል ህብረት እና የማክሮ ኢኮኖሚ ውህደትን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ሱክላል "የዶላር ዓለም የበላይነት ዘመን አብቅቷል፤ ይህ እውነታ ነው። ዛሬ ባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት አለን" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን ከሰሞኑን አስታውቃለች።