በቫይረሱ የተያዙ 5 ሰዎች በመልካም ጤንነት ላይ ሲሆኑ 74 ሰዎች ከለይቶ ማከሚያ ወጥተቃል
በቫይረሱ የተያዙ 5 ሰዎች በመልካም ጤንነት ላይ ሲሆኑ 74 ሰዎች ከለይቶ ማከሚያ ወጥተቃል
በሁሉም ወደ ሀገር መግቢያ ጣቢያዎች እየተደረገ የሚገኘው ምርመራ የተጠናከረ ሲሆን 600,080 በሙቀት መለያ (ኢቦላና ኮቪድ-19 በማጣመር) ማለፋቸውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡
በሙቀት መለያ ካለፉት ውስጥ 8,985 ሰዎች በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሃገራት የመጡ ናቸው፡፡
በሽታው ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት ከመጡ ተጓዦች በተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ 5 ግለሰቦች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው 992 ሰዎች ባሉበት ቦታ ለ14 ቀናት የሚቆይ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
አሁን ላይ 1285 የሚሆኑት ደግሞ ለ 14 ቀን የጤና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው ጤንነታቸው በመረጋገጡ የጤና ክትትላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
የበሽታውን ተመሳሳይ ምልክቶች በማሳየታቸው እንዲሁም ከመጀመሪያ ታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት 113 ተጠርጣሪዎች በተለያየ ጊዜ በለይቶ መቆያ ማእከል እንዲቆዩና የላብራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ 74ቱ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡
አምስቱ (5) የኮሮና ቨይረስ የተገኘባቸው ታማሚዎች በለይቶ ማቆያ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ያለው ኢንስቲትዩቱ ሰላሳ አራቱ (34) ተጠርጣሪዎች በለይቶ ማቆያ ሆነው የለቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣጠር መንግስት ትምህርት ቤቶችን፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ስብሰባዎችን ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ በማድረጉ ይታወቃል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ትኩረት መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች
● ሳል ወይም ትኩሳት ካለው ግለሰብ ቢያንስ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት ያህል መራቅ
● እጅዎን በአግባቡ ሳይታጠቡ አይንና አፍንጫዎን አይንኩ
● ከሰዎችጋር አይጨባበጡ
● እጅን በንጹህ ውሃና ሳሙና አዘውትረው ይታጠቡ
● ሰዎች ወደ በሚበዙባቸው ቦታዎች በተለይም የህመም ስሜት ካልዎት አይሂዱ
● በሚያነጥሱበት እና በሚያስሉበት ጊዜ አፍና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም ክርንዎን አጥፈው በመጠቀም ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ ይጠንቀቁ፣ የተጠቀሙበትን ሶፍትና ተመሳሳይ ነገሮች በቆሻሻ ክዳን ባላቸው ማጠራቀሚያ ያስወግዱ
● በስራ ቦታ፣በትራንስፖርት እና መኖሪያ ወይም የመኝታ ክፍል መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር ያድርጉ
● መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበል፣ የተሳሳቱ መረጃዎች የሚያስከትሉትን መደናገር እና ፍርሀት ይከላከሉ
●በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሀገራት የሚመጡ ሰዎች ወይም ንክኪ ያላቸው ማንኛወም ግለሰብ አራሱን ለ 14 ቀን በመለየት በበሽታው አለመያዛቸውን ሲያረጋግጡ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ይመከራል
ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻ ephieoc@gmail.com በመጠቀም መረጃ ማግኘት እና ጥቆማ መስጠ ይቻላል ሲል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትገልጿል፡፡