በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ ያለበት የመጀመሪያው ሰው ተገኘ
በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ ያለበት የመጀመሪያው ሰው ተገኘ
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ በቫይረሱ የተያዘ ግለሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን አረጋግጠዋል፡፡
ግለሰቡ፣ የ48 አመት የጃፓን ዜጋ ሲሆን፣ የካቲት 25/ 2012 ዓ/ም ከ ቡርኪና ፋሶ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ መግለጫ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ታማሚው፣ አስቀድሞ በተዘጋጀው የለይቶ ማከሚያ፣ ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ የከፋ የጤና እክል እንዳልገጠመው የተገለጸ ሲሆን ከበሽተኛው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸውን ግለሰቦችም የመለየትና ክትትል የማድረግ ስራ ተጀምሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ፣ ቫይረሱን ለመከላከል የተጀመሩትን እርምጃዎች እንድናጠናክር እንጂ እንድንደናገጥ ሊያደርገን አይገባም ሲሉ መግለጫውን የሰጡት ባለስልጣናት ተናግረዋል።
መደናገጥ እና አጉል ፍራቻ፣ ከበሽታው እኩል አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ያሉት ባለስልጣናቱ፣ በዚህ በሽታ የሚያዝ አብዛኛው ሰው፣ ቀላል ህመም ከያዘው በኋላ እንደሚድን ገልጸዋል። ነገር ግን እድሜያቸው በገፉ ወይም ተጨማሪ በሽታ ባላቸው ሰዎች ላይ፣ህመሙ የከፋ ሊሆን ይችላልም ነው ያሉት።
የኢትየጲያ መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር፣ በሽታው ቻይና ከተገኘበት ወቅት ጀምሮ፣ ቫይረሱ ወደ አገር እንዳይገባ፣ ከገባም ጉዳቱን ለመቀነስ፣ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ብሄራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ተቋቁሞ፣ የመከላከል ጥረቱን እየመራ ይገኛል። በተጨማሪም፣ በጤና ሚኒስቴርና በህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የሚመራ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉት የቴክኒክ ግብረ ሃይል ቅንጅታዊ አሰራሩን እየመራ ይገኛል።
መንግስትም፣ የበሽታውን አሳሳቢነት በመረዳት 300 ሚሊዮን ብር በጀት የመደበ ሲሆን ተጨማሪ በጀት እያፈላለገ እንደሚገኝም ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።
ለበሽታው መካላከል ሲባል፣ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ውስጥ የድንገተኛ ኦፕሬሽን ማእከል ተቋቁሞ፣ ሃያ አራት ሰአት እየሰራ ይገኛል እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ ዶ/ር ኤባ ናቸው።
በዚህ በሽታ ለተጠረጠሩ ግለሰቦች ማቆያ የሚሆኑ የተለዩ የጤና ተቁማት የተዘጋጁ ሲሆን የታመሙ ሰዎችን ለማከምም፣ የካ ኮተቤ ሆስፒታል አስፈላጊው የህክምና መሳሪዎች እና ባለሙያዎች ተሟልተውለት ዝግጅቱን አጠናቋል ተብሏል።
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ማህበረሰቡ ሊያደርግ የሚገባው ጥንቃቄ፡-
● ሳል ወይም ትኩሳት ካለው ግለሰብ ቢያንስ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት ያህል መራቅ
● እጅዎን በአግባቡ ሳይታጠቡ አይንና አፍንጫዎን አይንኩ
● ከሰዎችጋር አይጨባበጡ፣
● እጅን በንጹህ ውሃና ሳሙና አዘውትረው ይታጠቡ፣
● ሰዎች ወደ በሚበዙባቸው ቦታዎች በተለይም የህመም ስሜት ካልዎት አይሂዱ፣
● በሚያስነጥሱበት እና በሚያስሉበት ጊዜ አፍና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም ክርንዎን አጥፈው በመጠቀም
ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ ይጠንቀቁ፣ የተጠቀሙበትን ሶፍትና ተመሳሳይ ነገሮች በቆሻሻ ክዳን ባላቸው
ማጠራቀሚያ ያስወግዱ፣
● በስራ ቦታ፣በትራንስፖርት እና መኖሪያ ወይም የመኝታ ክፍል መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር
ያድርጉ፣
● መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበል፣ የተሳሳቱ መረጃዎች የሚያስከትሉትን መደናገር እና
ፍርሀት እርሶም ይከላከሉ!
የበለጠ መረጃ ሲያስፈልግ ነጻ በሆነው 8335 የስልክ መስመር ላይ መደወል ይቻላል፡፡