ምርጫ ቦርድ ዛሬ መዘጋቱን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን አረጋገጡ
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ለ15 ቀናት ዝግ እንዲሆኑ መንግስት ወስኗል
ቦርዱ የተዘጋው በቦርዱ በሚሰራ ደቡብ አፍሪካዊ ላይ የበሽታው ምልክቶች መታየታቸውን ተከትሎ ነው
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ተዘግቷል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ዛሬ ዝግ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ለአል ዐይን አረጋግጠዋል፡፡
ከዚሁ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ትምህርት ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ለ15 ቀናት ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ መንግስት አስታውቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በኩል ተመድቦ በቦርዱ እየሰራ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው የበሽታው ምልክት ታይቶበት ለሕክምና መሄዱ ነው ለመዘጋቱ ምክንያት የሆነው፡፡
በተመሳሳይ የምርጫ ቦረድ አባል የሆኑት ዶ/ር ጌታሁን ካሳ መዘጋቱን አረጋግጠው፣ የሚዘጋው ለዛሬ ብቻ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የቫይረሱ ምልክት የታየበት ግለሰብም የከፋ ነገር እዳልሆነ ሀኪሞች ማረጋገጣቸውን ዶ/ር ጌታሁን ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ በፌስ ቡክ ገጹ “ግለሰቡ ከአንድ ወር በፊት ወደ አገር ውስጥ የገባ ሲሆን ቦርዱም ምልክቶቹ ከታዩበት ጊዜ አንስቶ ምርመራ እንዲደረግለት ጠይቆ ምርመራው እንዲካሄድ እየጠበቀ ይገኛል” ያለ ሲሆን የቦርዱ ሰራተኞች በዛሬው እለት ከቤት ሆነው እንዲሰሩ ቦርዱ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታታ በማሰብ ትምህርት ቤቶች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትላልቅ ስብሰባዎች 15 ቀናት እንደሚዘጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አህመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መጋቢት 4፣ 2012 በሰጡት መግለጫ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መኖሩን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ግለሱቡ ጃፓናዊ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የገባው የካቲት 25 መሆኑንና ከእሱ ጋር ንክኪ ያላቸው 25 ሰዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን በቫይረስ ተያዙ ሰዎች ቁጥር 5 ሲደርስ፣ በለይቶ ማቆያ ቦታ ደግሞ 117 ሰዎች የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡