በ6 ወራት በኢትዮጵያ ላይ ከ2000 በላይ የሳይበር ጥቃቶችና ሙከራዎች ተደርገዋል- ኢንሳ
ባለፉት ስድስት ወራት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ኢንሳ አስታውቋል
ባንኮች፤ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ሚዲያዎች የሳይበር ጥቃቱ ኢላማ ካደረጋቸው ተቋማት መካከል ናቸው
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በ2015 በግማሽ ዓመት ቢደርሱ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከ2000 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተሰንዝረው ነበር ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ በ2015 ዓ.ም በጀት አመት በመጀመሪያው አጋማሽ በሀገራች 2,145 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች መፈጸማቸውን አስታውቀዋል
- የግድቡን ሙሌት ለማደናቀፍ በ37 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ ተነጣጥሮ የነበረ የሳይበር ጥቃት ማከሸፍ ተችሏል
- ኢትዮጵያ ፌስቡክንና ትዊተርን በሀገራዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የመተካት እቅድ እንዳላት አስታወቀች
ከተፈፀሙ የሳይበር ጥቃት እና ሙከራዎች መካከልም 2 ሺህ 49 ምላሽ የተሰጠባቸው ናቸው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ የተቀሩት በሂደት ላይ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም በመንፈቅ ዓመቱ የሳይበር ጥቃት ሙከራን የመመከት አፈፃፀም 91.5 ከመቶ ማድረስ መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
የተሞከሩ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ የመሰረተ-ልማቶችን ማቋረጥ፤ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሰሩ በማድረግ፣ የግንኙነትን መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበር እና በመውሰድ ጉዳት ይከሰት ነበር ብለዋል።
የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ ትኩረታቸዉን በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ነበሩ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት፣ ሚዲያ ተቋማት፣ ሚኒስቴር መስራቤቶች፣ የህክምናና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቃት ዒላማዎች እንደነበሩ አንስተዋል።
በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች መካከል የድረገጽ ጥቃት፣ ማልዌር፣ የመሰረተ ልማት ቅኝት፣ የመሰረተ ልማት ማቋረጥ፣ ሰርጎ መግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸዉ ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸዉ እንደነበሩ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
እንደ አጠቃላይ አስተዳደሩ ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በማስቆም፣ እንዲሁም አደገኛ የደህንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቆጣጠር ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ማዳኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ጥቃቶቹን በመከላከልም ሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችል አስራ አምስት ቢሊዮን ብር ከኪሳራ ማዳን መቻሉን መግለጻቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያኘነው መረጃ ያመለክታል።