በ3 ወራት በኢትዮጵያ ላይ ከ1 ሺህ 600 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መካሄዳቸውን ኢንሳ አስታወቀ
3ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ዛሬ ተጀምሯል
በ2014 በኢትዮጵያ ላይ በአጠቃላይ 8 ሺህ 900 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገው ነበር
የ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 1,613 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በኢትዮጵያ ላይ መደረጋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
ከጥቅምት 1/2015 እስከ ጥቅምት 30/2015 ዓ/ም ድረስ በሚካሄደው 3ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የመክፈቻ መርሃ ግብር በዛሬው እለት ተካዷል።
"የተቀናጀ የሳይበር ደህንነት ለሃገር ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር መክፈቻ ላይም ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ሌሎችን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሳይበር ጥቃት እያደረገ መምጣን አስታውቀዋል።
በ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በኢትዮጵያ ላይ 1 ሺህ 613 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መካሄዳውን ያስታወቁ ሲሆን፤ ባሳለፍነው የ2014 ደግሞ አጠቃላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራ 8 ሺህ 900 እንደሆነ አስታውሰዋል።
በ2012 ዓ.ም አጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ የተሞከረዉ የሳይበር ጥቃት 1 ሺህ 80 ብቻ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2013 ዓ.ም ወደ 2 ሺህ 800 ከፍ ማለቱን እና ይህም የሚደረጉ የሳይበር ሙከራዎች ከጊዜ ወደ ጊዝ እያደጉ መምጣቻቸወን ያመለክታል ብለዋል።
የ2014 ዓ.ም አጠቃላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራ 8 ሺህ 900 ሲሆን፤ ከቀዳሚዎቹ ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2012 ዓ.ም አንጻር በስምንት እጥፍ፤ ከ2013 ደግሞ መጠኑ በ3 እጅ ማሻቀቡንም አመላክተዋል።
በአሁኑ ጊዜ የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ከሚፈታተኑት አበይት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያን የሳይበር ሉአላዊነት ለማስጠበቅ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ዘላቂ በሆነ መልኩ ከማሳደግ ባሻገር የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
3ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ያሉ የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን መቀነስ፣ በዘርፍ የግሉን ሴክተር ሚና ማሳደግ እና ማበረታታት፣ በቂ እና ጥራት ያለው የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎችን ማፍራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንዲሁም የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤን ማሳደግ እንደሆነም ጠቅሰዋል።