ተቋማት ወደፊት ከሚገጥሟቸው 10 ዋና ዋና አደጋዎች መካከል የዲጂታል ስርዓት-መፈረካከስ እና የሳይበር ጥቃት ይገኙበታል
የሳይበር ወንጀሎች በያዝነው የፈረንጆቹ 2020 ከቀዳሚ የዓለም ስጋቶች መካከል እንደሆኑ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ሪፖርት ጠቆመ
በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ተቋማት ከሚያጋጥሟቸው 10 ዋና ዋና አደጋዎች መካከል የዲጂታል ስርዓት-መፈረካከስ እና የሳይበር ጥቃት አደጋዎች እንደሚገኙበት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም "World Economic Forum (WEF)" በሪፖርት ይፋ አደረገ።
ዓመታዊው የአለም አቀፍ የስጋት አደጋ ሪፖርት ከተቋማት መሪዎች፣ ከአካዳሚክ ምሁራን እና ከሌሎች በዓለም ዙሪያ ካሉ ሌሎች አካላት ከተደረጉ ቃለ-መጠይቆች የተጠናከረ መሆኑን ተነግሯል፡፡
በፈረንጆቹ 2020 የአየር ንብረት ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው ቢሆንም ከሳይበር ጋር ተያያዥነት ያላቸው አደጋዎች ለዓመታት እንዳደረሱት ጉዳት ሁሉ አሁንም ከፍተኛ ስጋት ሆነው እንደሚቀጥሉ ተገልጻል፡፡
በዚህ ጥናት ከተሳተፉት 76 ከመቶ የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች በ2020 የሳይበር ጥቃቶች የአገልግሎት ዘርፍ እና ወሳኝ መሠረተ-ልማቶች እንቅስቃሴ ያደናቅፋሉ ያሉ ሲሆን 75 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ የበይነ-መረብ ቀጥታ አገልግሎት ላይ የሚፈጸም ጥቃት እና የፋይናንስ ስርቆቶችን /online data and financial theft/ በቀጣይነት ይከሰታሉ ብለዋል፡፡
የሳይበር ጥቃቶች በመጪዎቹ አስርት ዓመታት ውስጥ ከሚፈጥሩት ተፅዕኖ አንፃር ከ10 ቀዳሚ አደጋ ሰንጠረዥ ውስጥ የተቀመጡ ሲሆን፣ የዴታ ስርቆት እና ማጭበርበር ደግሞ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተቀምጠዋል፡፡
በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ቴክኖሎጂዎች ላይ ለማህበረሰቡ እና ለዓለም ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታዎችን እያመጡ ቢሆንም ቴክኖሎጂው ያልታሰበ የሳይበር-አደጋ ተጋላጭነት እንዲሰፋ ማድረጉን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
ውጤታማ እና የተቀናጀ ዓለም አቀፍ የሳይበር-አስተዳደር ማዕቀፍ አለመኖር የኳንተም ኮምፒውቲንግ ፣ 5 ጂ ፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ከበይነ-መረብ ጋር ንክኪ ያላቸው ቁሶች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ተቀምጠዋል፡፡
በሳይበር ወንጀል የተሰማሩ አካላትን እንቅስቃሴ በማስቆም ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶችን ጉዳት ማስቆም ብቻ በቂ አለመሆኑን እና የሳይበር ወንጀለኞቹ የጥቃት አሻራቸውን በተቋሞቻችን ላይ እንዳያሳርፉ በመከላከል የዴታ ስርቆት፣ የፋይናንስ ነክ አደጋዎችን እንዲሁም በቁሳዊ መገልገያዎቻችን ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ነቅቶ መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ተገልጿል፡፡