የአፍሪካ ህብረት ከአዲሱ የኮሮና ዝርያ ጋር በተያያዘ ሃገራት ተቻኩለው የጉዞ እገዳ መጣላቸውን ተቃወመ
ክትባቱን አጠናክሮ መቀጠሉ እንደሚበጅም ነው ማዕከሉ ያስታወቀው
አፍሪካ ሲዲሲ ጉዞዎችን ከማገድ ይልቅ በመረጃ ልውውጥና በሌሎችም መንገዶች መረዳዳቱ እንደሚጠቅም አስታውቋል
‘ኦሚክሮን’ ከተባለው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ጋር በተያያዘ ሃገራት ተቻኩለው የጉዞ እገዳዎችን መጣላቸውን የአፍሪካ ህብረት ተቃወመ፡፡
በህብረቱ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ የጉዞ እገዳዎች የቫይረሱን ስርጭት እንደማይገቱ ከአሁን ቀደምም አይተናል ብለዋል፡፡
ከእገዳ ይልቅ ቫይረሱን የተመለከቱ መረጃዎችን መለዋወጡ እና ከአሁን ቀደምም የነበሩ የጥንቃቄ መንገዶችን መተግበሩ እንደሚጠቅምም ተናግረዋል፡፡
ክትባቱን አጠናክሮ መቀጠሉ እንደሚበጅም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
ደቡብ አፍሪካ የተጣለብኝ የጉዞ ክልከላ “በጉልበት የተጫነና የማይጠቅም ነው” ስትል ተቃወመች
“ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሃገራት በሚጓዙ ሰዎች ላይ የጉዞ እገዳን መጣሉን ማዕከላችን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ ተጓዦች ላይ እገዳ መጣሉ ትርጉም ያለው ውጤት እንዳላስገኘም በተጨባጭ ተመልክተናል”ም ብለዋል ንኬንጋሶንግ ጥድፊያውን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ።
ንጽህናን እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማድረግ ለሚሉት የጥንቃቄ መንገዶች ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል፡፡
ይህ የዶ/ር ንኬንጋሶንግ መግለጫ የዓለም ጤና ድርጅት ‘ኦሚክሮን’ በሚል ይጠራ ያለለት አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በደቡብ አፍሪካ መገኘቱ ከታወቀ ከሁለት ቀናት በኋላ የወጣ ነው፡፡
የቫይረሱ አዲስ ዝርያ የመገኘቱ ዜና ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ሃገራት በተለይም አሜሪካን ጨምሮ ጀርመንና እንግሊዝን መሰል ምዕራባዊ ሃገራት ከደቡብ አፍሪካ እና ከስድስት ጎረቤት ሃገራት በሚጓዙ ዜጎች ላይ እገዳዎችን ለመጣል አላመነቱም፡፡
ካናዳ፣ ሞሮኮ፣ ሩሲያ እና ሌሎች ሃገራትም እገዳውን ከጣሉ ሌሎች ሃገራት መካከል ናቸው፡፡
ይህ ሊሆን አይገባም ያለችው ደቡብ አፍሪካ መተባበሩ ቢቀድም ስትል ጠይቃለች፡፡