“በቀብሩ” ላይ በሄሊኮፕተር የተገኘው ቤልጂየማዊ
የ45 አመቱ ጎልማሳ ረስተውኛል ያላቸውን ቤተሰቦቹን በአካል ለማግኘትና “የህይወት ትምህርት ለመስጠት” ሞቱን አውጇል
በቀብሩ ላይ የተገኙ ቤተሰብና ወዳጆቹንም ይቅርታ ጠይቆ “ሳንሞት መጠያየቁ” ይሻላል ብሏቸዋል
የ45 አመቱ ቤልጂየማዊ ዴቪድ ባርተን የናፈቁትን ቤተሰቦቹን በአንድ ላይ ለመሰብሰብ ብቸኛው መንገድ “ሞቱን ማወጅ” መሆኑን አምኖበታል።
ይህን እቅዱንም ለሚስቱና ለልጆቹ ያዋይና እንዲገፋበት ያበረታትቱታል።
አንደኛዋ ልጁም በማህበራዊ ትስስር ገጿ ላይ “በሰላም እረፍ አባቴ፤ አለም ፍትሃዊ አይደለችም፤ አያት ላደርግህ እኮ ነበር፤ ሞት ግን ቀድሞ ነጠቀኝ” የሚል መልዕክት ታሰፍራለች።
ይህን መልዕክት የተመለከቱ ወዳጅ ዘመዶችም አንዱ ለአንዱ እየደወለ የዴቪድን ህልፈት አስተጋቡት።
በቤልጂየሟ ሌጅ ከተማም ስርአተ ቀብሩ የሚፈጸምበት ስፍራና ቀን ተገልጾ ድራማው ይቀጥላል።
ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ እርሙን ማውጣት እንደጀመረ ግን ዴቪድ ከሄሊኮፕተር ላይ ወርዶ ለቀስተኛውን ማጽናናት ጀመረ።
በቲክቶክ ከ165 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የ45 አመቱ ጎልማሳ በራሱ ያሟረተው ቤተሰቦቹን ሁነኛ ትምህርት ለመስጠት በማለም እንደሆነ ተናግሯል።
“ቤተሰቦቼ ጠይቀውኝም ሆነ እንድጎበኛቸው ጋብዘውኝ አያውቁም፤ ተለያይተን ነው የኖርነው፤ ይህ ሁሌም ምቾት አይሰጠኝም፤ እናም ለመሰባሰብ ሀዘንን ብቻ መጠበቅ እንደሌለባቸው ላስተምራቸው በሀሰት ሞቻለሁ” ብሏል።
የዴቪድ በቀብሩ ላይ በሄሊኮፕተር የመከሰት ጉዳይ በቤተሰብና ወዳጆቹ ዘንድ ድንጋጤ፣ ደስታ እና ንዴት የተቀላቀለበት ስሜትን ፈጥሯል ይላል ሚረር በዘገባው።
ዴቪድ ሊቀብሩት የመጡ ቤተሰቦቹን እየዞረ በመጨበጥ “እንኳን ደስ ያላችሁ፤ አልሞትኩም” እያለ የሞት ድራማው ያስገኘውን በረከት ለመዘርዘር መሞከሩም ያበሳጫቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አልነበሩም ተብሏል።
“እንዴት በሞት ይቀለዳል” በሚል ቅሬታቸውን የገለጹለት ሲሆን፥ አብዛኛው ግን የዴቪድ ህልፈት ውሸት መሆኑ ደስታን ፈጥሮባቸዋል ይላል ዘገባው።
“በቀብሬ ላይ የተገኙት ከቤተሰቦቼ ግማሾቹ ቢሆኑ ነው፤ ማን ለኔ ቦታ እንዳለውም ተመልክቸበታለሁ” ያለው የ45 አመቱ ጎልማሳ የቀረበው ቅሬታ ተገቢነትን ቢያምንበትም ቁምነገሩን ያዙልኝ ብሏል።
ከልጅና ሚስቱ ጋር የከወነው የተዋጣለት ድራማ በመላው አለም በስራና በህይወት ምክንያት የተረሳሱ ወዳጅ ዘመዶችን ያነቃል የሚል እምነትም አለው።