ኢራን በእስራኤል የምትፈጽማቸው አደገኛ የስለላ ተልዕኮዎች
የቴሄራን የደህንነት አባላት ባለፈው አንድ ወር እስራኤላውያን ዜጎችን ለስለላ በበይነ መረብ ስትመለምል እንደነበር ተሰምቷል
ሀገሪቷ እስራኤላውያን ዜጎች ለምታሰማራባቸው የተለያዩ ተልዕኮዎች እስከ 100 ሺህ ዶላር ድረስ ትከፍላለች ነው የተባለው
በኢንተርኔት ምልመላ ኢራን በእስራኤል የምታሰማራቸው ሰላዮች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የእስራኤል የደህንነት ተቋማት አስታውቀዋል፡፡
ቴሌግራምን ጨምሮ የተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም የቴሄራን የደህንነት አባላት እስራኤላውያን ዜጎችን በመመልመል ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ተልዕኮዎችን እንደሚያስፈጽሙ ተነግሯል፡፡
የደህንነት አባላቱ ከተመልማዮቹ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ሊጠለፍ የማይችል ስልክ ፣ የጦር መሳርያ እና ሌሎችንም ግበአቶች እንዲገዙ ትዕዛዝ ከመስጠት ባለፍ ተልዕኮዎችን እንዲፈጽሙ በማማከር እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
በቀጠናው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ በሚገኝበት በዚህ ወቅት እየተደረጉ የሚገኙ የስለላ ተልዕኮዎች በመንግስት ላይ ተቃውሞ ከማስነሳት ጀምሮ የተለያዩ ሰዎች ላይ ግድያ እስከመፈጸም ይደርሳል፡፡
ከነዚህ ውስጥ የእስራኤል የደህንነት ባለስልጣናት በክትትል የደረሱበት የ35 አመቱ እስራኤላዊ ቭላድሚር ቬርኮቭስኪ ታሪክ አንዱ ነው፡፡
በማዕከላዊ እስራኤል ፔታቲቲክቫ ነዋሪ የሆነው ቬርኮቭስኪ ስሙ ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የእስራኤል ሳይንቲስትን ለመግደል ተልዕኮ ተቀብሎ ሲንቀሳቀስ ተደርሶበታል፡፡
የቴልአቪቭ የደህንነት ባለስልጣናት እንዳሉት በቅርብ ወራት ኢራን በተለያዩ ሳይንቲስቶች እና ወታደራዊ መሪዎች ላይ ግድያ ሙከራ ለማድረግ ተልዕኮዎችን እየሰጠች ትገኛለች፡፡
ከቬርኮቭስኪ በፊትም ባለፈው አንድ ወር ሁለት ተመሳሳይ ተልዕኮዎችን የተቀበሉ እስራኤላውያን በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በእስራኤል ፖሊስ ውስጥ የሀገር ውስጥ ጸጥታ እና ድህንነት ክፍል አዛዥ ማኦር ጎሬን “በተለያዩ ጊዜያት ለስለላ በውጭ ሀገራት የተመለመሉ ዜጎች እና ተልእኮ ቢገጥመንም ቭላድሚር ቬርኮቭስኪ ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ የነበረው ግን በአይነቱ ጠንከር ያለ ነው” ብለዋል፡፡
ቬርኮቭስኪ አንድ እስራኤላዊ ከፍተኛ ሳይንቲስት ለመግደል የ100 ሺ ብር ክፍያ ለመቀበል ተስማምቶ ሽጉጥ ከነሙሉ ጥይቱ ታጥቆ ግድያውን ከፈጸመ በኋላ ወድያው ከሀገር ለመውጣት የሚያስችለውን ሙሉ ዝግጅት አጠናቆ እንደነበር ተደርሶበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሀገር ክህደት በቀረበበት የክስ መዝገብ ላይ በተገለጸው መሰረት ቬርኮቭስኪ ከኢራናዊ ወኪል ጋር በቴሌግራም የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ በኩል ተገናኝቷል፣ በመካከላቸው የነበረው ግንኙነትም በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተደረገ ነበር፡፡
ተጠርጣሪው “ከጠላት” አካል ጋር እየተገናኘ መሆኑን እንደሚያውቅ ግድያውን ለመፈጸም ከመዘጋጀቱ በፊትም በኢራኑ የደህንነት አባል አማካኝነት ከነሀሴ እስከ መስከረም የተሰጡትን ቀለል ያሉ ተልዕኮዎች መፈጸሙን አምኗል፡፡
ከነዚህ መካከል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁን የሚቃወሙ መፈክሮችን በቴልአቪቭ ማሰራጨት የመከታተያ መሳርያዎችን በተለያ ስፍራዎች ላይ ማስቀመጥ እና ሌሎች በመንግስት ላይ ተቃውሞን የሚያንሰሱ ድርጊቶችን ፈጽሟል ነው የተባለው፡፡
ዋነኛ የተባለውን የሳይንቲስት ግድያ ከመፈጸሙ በፊት በጸጥታ ሀይሎች ቁጥጥር ስር የዋለው ተከሳሽ ከዚህ ቀደም ለነበሩት ተልዕኮዎች በሙሉ በዲጂታል የክፍያ መንገድ ገንዘብ መቀበሉንም አምኗል፡፡
“የጥፋት ልዑካንን በእስራኤል ውስጥ በማሰማራት ኢራን ቀይ መስመሩን ጥሳለች” ያሉት የእስራኤል የደህንነት ተቋማት፤ በገንዘብ በመታለለም ሆነ ባለማወቅ በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎች ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አውቀው ከዚህ ድርጊት ራሳቸውን እንዲያርቁ አስጠንቅቀዋል፡፡