ታሊባን የአፍጋኒታን ሚዲያዎች ሰውን ጨምሮ በህይወት ያሉ ፍጡራንን እንዳያሳዩ እገዳ ጣለ
የአፍጋኒስታን ሚዲያዎች ስራቸውን እንዴት መቀጠል እንዳለባቸው ግራ ገብቷቸዋል ተብሏል
በታሊባን የምትመራው አፍጋኒስታን ከዚህ በፊት አነጋጋሪ ህጎችን ማውጣቱ ይታወሳል
ታሊባን የአፍጋኒታን ሚዲያዎች ሰውን ጨምሮ በህይወት ያሉ ፍጡራንን እንዳያሳዩ እገዳ ጣለ፡፡
አፍጋኒስታንን እየመራ ያለው ታሊባን መራሹ መንግስት የሀገሪቱ ሚዲያዎች በህይወት ያሉ ማናቸውም ፍጡራን ምስሎችን እንዳያስተላልፉ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ ከሆነ የአፍጋኒስታን ሚዲያዎች የሰው ልጆችን ጨምሮ ማናቸውንም ፍጡሮች በህይወት እያሉ ምስላቸውን እንዳያስተላልፉ ታግደዋል፡፡
እገዳው በተለይም ቴሌቪዥን፣ ድረገጾች እና ጋዜጦችን ይጎዳል የተባለ ሲሆን ስራቸውን እንዴት መቀጠል እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል ተብሏል፡፡
ህጉ የወጣው የእስልምና ህግን መሰረት በማድረግ ነው የተባለ ሲሆን ታሊባን መራሹ መንግስት ደግሞ በሸሪዓ የሚመራ መንግስት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአዲሱ ህግ መሰረትም በአፍጋኒስታን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በየጊዜው እየተሸረሸረ ስለመምጣቱ ማሳያ ነውም ተብሏል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ ሳይፉል ኢስላም ካይባር ለኤኤፍፒ እንዳሉት የመንግስት ተቋማት የሆኑትን ጨምሮ ሁሉም ሚዲያዎች ሰዎችን እና እንስሳትን ጨምሮ በህይወት ያለ ፍጡሩ ምስል እንዳያሳዩ ተነግሯቸዋል ብለዋል፡፡
የታሊባን የጸጥታ ሀይል ጺም አላሳደጉም ያላቸውን 281 አባላቱን ከስራ አገደ
ይሁንና አዲሱ ህግ በአፍጋኒስታን የሚሰራጩ የውጭ ሀገራት ሚዲያዎችን ስለማካተቱ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ቀስ በቀስ ይተገበራል የተባለው አዲሱ ህግ መሰረቱ የእስላማዊ ስርዓት ወይም ሸሪዓ ህግ ነው ቢባልም በዚህ የረጅም ዓመታት ልምድ ላቸው ሳውዲ አረቢያ እና ኢራን መሰል ህግ አውጥተው አያውቁም፡፡
ታሊባን ከዚህ በፊት የጸጥታ ሀይሎች ጺማቸው እንዳያላጩ፣ ሴቶች ከቤታቸው ውጪ ፊታቸውን እንዲሸፈኑ፣ ጮክ ብለው እንዳይናገሩ እና ሌሎች ክልከላዎችን ማድረጉ አይዘነጋም፡፡