አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ልዑክ ስራ ከመጀመሩ በፊት ግብጽ በሶማሊያ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን እያገዘች እንደሆነ ተነገረ
ካይሮ ለሞቃዲሾ የጦር መሳርያ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ተጨማሪ 7 ሺህ ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ መላኳ ተሰምቷል
የአልሲሲ መንግስት በሶማሊያ የወሰደው እርምጃ እና ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት እያሳደገ መምጣቱ በኢትዮጵያ ላይ ጫና የመፍጠርያ አንድ አካል እንደሆነ ነው ተብሏል
ግብጽ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክ (አትሚስ) የሰራ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈች እንደምትገኝ ተነገረ፡፡
ካይሮ የሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎች ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ታጣቂዎች ለመዋጋት በሚያደርጉት ጥረት ስልጠና እና ድጋፍ እየሰጠች እንደምተግኝ ዘ ናሽናል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ባሳለፍነው አመት ነሀሴ ወር ሶማሊያ እና ግብጽ የወታደራዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ግብፅ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጦር መሳሪያዎችን፣ወታደራዊ አማካሪዎችን፣ አሰልጣኞችን እና የፀረ ሽብር ኮማንዶዎችን ወደ ሞቃዲሾ ልካለች።
ከዚህ በተጨማሪ በመጪው ጥር ወር የስራ ጊዜው የሚጠናቀቀውን (አትሚስ) የሚተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) ውስጥ እስከ 5 ሺ የሚደርሱ ወታደሮቿን ለማሰማራት እየተጠባበቀች ትገኛለች፡፡
ዘ ናሽናል ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው በአሁኑ ወቅት 22 ሺህ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአትሚስ እና በሁለትዮሽ የጋራ ጸጥታ ስምምነት መሰረት በሶማሊያ ይገኛሉ፡፡
በግብጽ አማካሪዎች የሚደገፉ አንዳንድ የሶማሊያ የጸጥታ ሀይሎች የአትሚስ ቀነ ገድብ ከመጠናቀቁ በፊት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጦር ወደ ሶማሊያ እንዳታስገባ ለመከላከል በኢትዮጵያ ጦር የአቅርቦት መስመር ላይ መሰማራታቸው ተዘግቧል፡፡
ሆኖም ምንጮቹ እንደተናገሩት ካይሮ ለሞቃዲሾ የጦር መሳርያ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ተጨማሪ 7 ሺህ ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ መላኳን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
በአንጻሩ አትሚስን የሚተካው በመጪው ታህሳስ ስራ የሚጀምረው አዲስ ልዑክ ውስጥ የኢትዮጵያ ጦር እንዲሳተፍ እንደማትፈልግ እየገለጸች የምትገኝው ሞቃዲሾ ከካይሮ ጋር ያለት ትብብር እያደገ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
ግብፅም እና ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት ከአዲስአበባ ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ይገኛሉ፤ ካይሮ በኢትዮጵያ የሚገነባው የአባይ ግድብ የውሀ ድርሻየን ይቀንሳል በሚል ለአመታት ከኢትዮጵያ ጋር እየተወዛገቡ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በበየነ መረብ በተካሄደ የውሃ ኮንፈረንስ ላይ ግብጽ “የተከበረው የናይል ወንዝ ስጦታ ናት” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም “የአባይ ወንዝ በተለይ ከግብፃውያን ህይወት እና ህልውና ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል
ሶማሊያ በበኩሏ እንደግዛት አካሏ ከምትቆጥራት ከራስገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የወደብ ስምምነት ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ ከሚገኙ የቀጠናው ሀገራት ጋር ወዳጅነቷን እያጠበቀች ነው፡፡
ግብፅ በሶማሊያ ያላትን ወታደራዊ ሚና የምትነቅፈው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በጥር ወር የገባችውን ስምምነት የቀይ ባህር መዳረሻ የባህር ትራንስፖርትን ለመጠበቅ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያስችላል ስትል ስትከራከር ቆይታለች።
የአልሲሲ አስተዳደር በሶማሊያ የወሰደው እርምጃ እና ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት እያሳደገ መምጣቱ በግድቡ ላይ ስምምነት እንድታደርግ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እያደረገ የሚገኝው ሙከራ ሂደት ማሳያ አንድ አካል ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ከሶማሊያ እና የኤርትራ መሪዎች ጋር በአስመራ የተገናኙት ፕሬዝዳንት አልሲሲ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ሀገራቸው "ሶማሊያ ጸጥታ እና ደህንነቷን መመለስ እንድትችል ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ትሰጣለች" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡