ዘለንስኪ ሩሲያን ማሸነፍ ያስችላል ያሉትን "የድል እቅድ" ለፓርላማ ይፋ አደረጉ
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አነጋጋሪውን እና ሲጠበቅ የነበረውን የድል እቅድ በፓርላማ ቀርበው በዛሬው እለት ይፋ ማድረጋቸው ተገልጿል
ፕሬዝደንቱ ይፋ ያደረጉት የድል እቅዱ አምስት ነጥቦችን ያካተተ ነው ተብሏል
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያን ማሸነፍ ያስችላል ያሉትን "የድል እቅድ" ለፓርላማ ይፋ አደረጉ።
ዘለንስኪ አነጋጋሪውን እና ሲጠበቅ የነበረውን የድል እቅድ በፓርላማ ቀርበው በዛሬው እለት ይፋ ማድረጋቸውን ኪቭ ኢንዲፔንደንት የተባለው የሀገሪቱ የዜና ድረ ገጽ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ እቅዱ አምስት ነጥቦች ያሉት ሲሆን የተወሰኑ ክፍሎቹ አሁንም ሚስጥራዊ ናቸው።
ይህ እቅድ ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን ግብዣ እንዲቀርብላት፣ በሩሲያ መሬት ላይ ጥቃት መፈጸም እንድትችል እንዲፈቀድላት፣ ኑክሌር ያልሆነ ጥቃት መከላከያ እንዲኖራት፣ የኢኮኖሚ ትብብር እና ከጦርነት በኋላ የዩክሬይን ጦር በኔቶ ተጠባባቂ ጦር ውስጥ እንዲካተት የሚሉ ነጥቦችን ያካተተ ነው።
እቅዱ አሁንም ይፋ ያልሆኑ ሶስት ሚስጥራዊ አጀንዳዎች እንዳሉት ዘገባው ጠቅሷል።
የገዥው ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዴቪድ አርካሚኒ ሚስጥራዊ ጉዳዮቹ ለተቀናቃኞቹ ይቀርባሉ ብለዋል። "እቅዱ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ከቀጣይ አመት ሳይዘገይ ጦርነቱን ማቆም እንችላለን" ሲሉ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ የዩክሬን ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲይርስኪ፣ የወታደራዊ ደህንነት ኃላፊ ኪርይሎ ቡዳኖቭ እና ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ባሉበት ተናግረዋል።
የኔቶ አባልነት ግብዣው ከዝርዝሮቹ በቀዳሚነት የተቀመጠ ነው ተብሏል።
ኪቭ ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበችው መስከረም 2022 ቢሆንም እስካሁን ከአጋሮቿ ግልጽ ምላሽ አላገኘችም።
ዘለንስኪ እርምጃ መወሰድ ያለበት "አሁን" ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ነጥብ ጦርነቱን ወደ ሩሲያ ምድር መሳብ አስፈላጊነትን የሚያወሳ ሲሆን ሶስተኛው ነጥብ ደግሞ ሚስጥራዊ ክፍል ያለው ኑክሌር ያልሆነ የጥቃት መከላከያ ነው። ዩክሬን ወደፊት ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ራሷን ለመከላከል የሚያስችል "አጠቃላይ ኑክሌር ያልሆነ የመከላከያ ማዕቀፍ በግዛቷ እንዲኖር" ሀሳብ አቅርባለች።
ዩክሬን በዚህ የድል እቅዷ ከአሜሪካ እና የአውርፓ ህብረት ጋር በመሆን የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም እና ግዙፉ እና ልምድ ያለው ጦሯ በኔቶ ውስጥ እንዲሰማራ ሀሳብ አቅርባለች።
ሩሲያ በ2022 የጀመረችው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" 32 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን አሁንም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው።
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ያሉ አራት ግዛቶችን ሙሉ በሙሉ የራሳ የማድረግ እቅድ እንዳላት ስትገልጽ ዩክሬን በአንጻሩ የሩሲያ ኃይሎች ከግዛቷ እንዲወጡ ትፈልጋለች። የሁለቱ ወገኖች
ፍላጎት የተራራቀ በመሆኑ ምክንያት ጦርነቱን በሰላም ለማስቅም የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም።