ዳኒ አልቬስ በአራት አመት ከስድስት ወር እስራት ተቀጣ
የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች በቀረበበት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ነው ቅጣቱ የተላለፈበት
ብራዚላዊው ተጫዋች ለከሳሿ 150 ሺህ ዶላር እንዲከፍልም ተወስኖበታል
- የስፔን ፍርድቤት በጾታዊ ጥቃት ተከሶ በእስር ላይ በሚገኘው የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች ዳኒ አልቬስ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳለፈ።
የ40 አመቱ ብራዚላዊ በአራት አመት ከስድስት ወራት በእስር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
የቀድሞው ተጫዋች በታህሳስ ወር 2022 በባርሴሎና በሚገኝ የምሽት መዝናኛ ስፍራ ውስጥ አስገድዶ ደፍሮኛል በሚል ክስ ላቀረበችው እንስትም 150 ሺህ ዩሮ እንዲከፍልም ፍርድቤቱ ወስኗል።
ብራዚላዊው ተከላካይ በጥር ወር 2023 በቁጥጥር ስር ውሎ በእስር ላይ የሚገኘው ዳኒ አልቬስ በመጀመሪያ ክሱን ቢያስተባብልም በሂደት በፈቃደኝነት ወሲብ መፈጸማቸውን ማመኑ ይታወሳል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው አልቬስ ትዳሩን ከመፍረስ ለመጠበቅ ሲል ማስተባበሉንም መናገሩ አይዘነጋም።
የስፔን ፍርድ ቤት ተጫዋቹ ከጓደኞቹ ጋር በባርሴሎና የምሽት መዝናኛ ክበብ ውስጥ ያገኛትን የ23 አመት ወጣት ያለፈቃዷ አስገድዶ መድፈሩንና በሃይል ገፍትሮ እንደጣላት ማረጋገጡን ገልጿል።
በስፔን አስገድዶ መድፈር እስከ 15 አመት በሚያደርስ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን፥ አቃቤ ህግ አልቬስ በዘጠኝ አመት እስራት እንዲቀጣ ጠይቆ እንደነበር ስካይኒውስ ዘግቧል።
የተጫዋቹ ጠበቃ አልቬስ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።
ለባርሴሎና ከ400 ጊዜ በላይ የተሰለፈው አልቬስ ከካታላኑ ክለብ ጋር ስድስት የሊግ እና ሶስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል። በኳታር በተካሄደው የአለም ዋንጫም የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አባል እንደነበር ይታወሳል።