ዳኒ አልቬስ በ1 ሚሊየን ዩሮ ዋስትና ከእስር ሊለቀቅ ነው
ብራዚላዊው ተጫዋች ከተላለፈበት የአራት አመት ተኩል እስራት ሩቡን በእስር ቤት ማሳለፉን በመጥቀስ በዋስ እንዲፈታ ጠበቃው ጠይቋል
የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች ከእስር ቢለቀቅም ከስፔን እንዳይወጣ ፓስፖርቱን ይነጠቃል ተብሏል
የስፔን ፍርድ ቤት የቀድሞው የባርሴሎና እና ብራዚል ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ዳኒ አልቬስ በ1 ሚሊየን ዩሮ ዋስትና እንዲለቀቅ ወሰነ።
ፍርድቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው የአልቬስ ጠበቃ ተጫዋቹ ባለፈው ወር ከተላለፈበት የአራት አመት ተኩል እስራት ሩቡን በእስር ላይ ማሳለፉን በመጥቀስ ባቀረበው አቤቱታ ነው።
በባርሴሎና በሚገኝ የምሽት ክለብ ውስጥ አንዲት ወጣትን አስገድዶ ደፍሯል የሚል ክስ የቀረበበት አልቬስ ከጥር 2023 ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የስፔን ፍርድቤት በዛሬው እለት የአልቬስን አቤቱታ ተመልክቶ በ1 ሚሊየን ዩሮ ዋስትና እንዲለቀቅ መወሰኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ተጫዋቹ በየሳምንቱ ፍርድ ቤት እንዲቀርብና ከሳሿን በምንም አይነት መልኩ ለማግኘት እንዳይሞክርም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ብራዚላዊው ተጫዋች ከእስር ሲለቀቅ ከስፔን እንዳይወጣም የብራዚልና የስፔን ፓስፖርቱን ይነጠቃል ነው የተባለው።
የቀድሞው የባርሴሎና፣ ሲቪያ፣ ፒኤስጂ እና ጁቬንቱስ ተጫዋች በቀረበበት ክስ ሁሉም ፊቱን ሲያዞርበት የሀገሩ ልጅ ኔይማር ብቻ አጋርነቱን አሳይቶታል።
ኔይማር፥ አልቬስ ለከሳሹ እንዲከፍል የተላለፈበትን የ150 ሺህ ዩሮ ካሳ እንደሚከፍል ማሳወቁም አይዘነጋም።
ለባርሴሎና ከ400 ጊዜ በላይ የተሰለፈው አልቬስ ከካታላኑ ክለብ ጋር ስድስት የሊግ እና ሶስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በኳታር በተካሄደው የአለም ዋንጫም የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አባል እንደነበር ይታወሳል።