በአሜሪካ በ18 ወራት ውስጥ ከ500 ሺህ በላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መፈጸማቸው ተገለጸ
ከተደፈሩት አሜሪካዊያን ውስጥም ከ64 ሺህ በላይ በሚሆኑት ላይ እርግዝና ተፈጥሯል ተብሏል
በአሜሪካ ወጥ የሆነ የጽንስ ማቋረጥ መብትን የሚሰጥ ህግ አለመኖሩ ጭቅጭቅ አስነስቷል
በአሜሪካ በ18 ወራት ውስጥ ከ500 ሺህ በላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መፈጸማቸው ተገለጸ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር በሆነችው አሜሪካ ይፋ በተደረገ አንድ ጥናት ባለፉት 18 ወራት ውስጥ 520 ሺህ የአስገድዶ መደፈር ወንጀሎች መፈጸማቸውን ይፋ አድርጓል።
ጃማ የተሰኘው የጥናት ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት ከአራት እስከ 18 ወራት ውስጥ ባሉት ጊዜያት 520 ሺህ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞ በ64 ሺህ 525 ተጎጂዎች ላይ እርግዝና ተፈጥሯል።
ተፈጸሙ የተባሉት የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎቹ በ14 የአሜሪካ ግዛቶች ላይ ብቻ ያለውን የሚያሳዩ እንደሆነም በጥናቱ ላይ ተገልጻል።
በአሜሪካ ጽንስ የማቋረጥ መብትን የሚፈቅዱ ግዛቶች ውስን ሲሆን በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ በማንኛውም ምክንያት ይንስ እንዳይቋረጥ ይከለክላሉ።
በተወሰኑት የአሜሪካ ግዛቶች ተገደው የተደፈሩ እንስቶች ጽንስ ማቋረጥ ቢፈልጉም አገልግሎቱን እንደተከለከሉ ተገልጻል።
ጽንስ ማቋረጥ መብትን በተከለከሉ ግዛቶች የሚኖሩ አሜሪካዊያን ይንስ ማቋረጥ ፈቃድ ወዳለባቸው ሌሎች ግዛቶች ለመጓዝ ተገደዋልም ሲል ሲኤንኤን ጥናቱን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎም ጽንስ የማቋረጥ መብት ለሁሉም አሜሪካዊያን ሊፈቀድ ይገባል የሚል ተቃውሞ በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጥናቱ መሰረት 70 በመቶ አሜሪካዊያን አስገድዶ የተደፈሩ እና እርግዝና የተፈጠረባቸው ሴቶች ጽንስ የማቋረጥ መብት ሊፈቀድላቸው ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ተገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችም ተገደው የተደፈሩ ሴቶች ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ሌላ ግዛት እንዲጓዙ መደረግ እንደሌለበት እየተናገሩ ይገኛሉ።
እንዲሁም ለጤናቸው አስጊ እስካልሆነ ድረስ በፈለጉበት ጊዜ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት ማግኘት ይገባቸዋልም ብለዋል።
የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ የስነ ልቦና እና የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።