የሞሮኮና የፒ.ኤስ.ጂ ኮከብ አሽራፍ ሃኪሚ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሰሰ
የተጫዋቹ ጠበቃ ፋኒ ኮሊን በሃኪሚ ላይ የቀረበው ክስ "ውሸት" ነው ስትል ተናግራለች
ሃኪሚ ወንጀሉን የፈጸመው ከሳሹን ወደ ቤቱ አብራው እንድትሄድ “እከፍልሻለሁ” በሚል አግባብቶ ነው ተብሏል
የፈረንሳይ አቃቤ ህግ የፓሪስ ሴንት ዠርሜይንና የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድንተከላካዩ አሽራፍ ሃኪሚን በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ መሰረተበት።
በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ላሰየችው ብቃት ቁልፍ ሚና የነበረው ሃኪሚ፤ ደፈራት የተባለችው ሴት የ24 ዓመት እንስት መሆኗም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዓቃቤ ህግን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሃኪሚ ወንጀሉን የፈጸመው ባለቤቱ እና ልጆቹ ለእርፈት ወጣ ባሉበት ባለፈው ቅዳሜ ነው የተባለ ሲሆን፤ ከሳሹን በፓሪስ ቦሎኝ-ቢላንኮርት ከተማ ፓሪስ አካባቢ ወደሚገኘው ቤቱ አብራው እንድትሄድ “እከፍልሻለሁ” በሚል አግባብቶ ነው ተብሏል።
ተበዳይዋ እሁድ እለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄዳ ረቡዕ እለት በአቃቤ ህግ ጥያቄ እንደቀረበላትም ነው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች የገለጹት።
የተጫዋቹ ጠበቃ ፋኒ ኮሊን በሃኪሚ ላይ የቀረበው ክስ "ውሸት" ነው ስትል ተናግራለች። ክለቡ ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን ጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።
በፈረንሳይ ሕግ ክስ ተመሰረተ ማለት ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል ማለት አይደለም።
የፈረንሳዩ ሻምፒዮን ፒኤስጂ ረቡዕ እለት ወደ ጀርምን በማቅናት ከባየር ሙኒክ ጋር በቻምፒየንስ ሊግ 16 የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ያደርጋል።
ክለቦቹ በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሙኒክ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
እናም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰው ሃኪሚ በዚህ ጨዋታ ለመጫወት ከቡድን አጋሮቹ ጋር ፈረንሳይን ለቆ እንዲወጣ ይፈቀድለታል ወይስ አይፈቀድለትም ለሚለው በግልጽ የተባለ ነገር የለም።
በፒ.ኤስ.ጂ አስካሁን 73 ጨዋታዎችን በማድረግ ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱን የቀጠለው ሃኪሚ ቀደም ባሉ ዓመታት ለቡንደስሊጋውን ቦርሽያ ዶርትሙንድ ክለብ በመጫወት ብቃቱን ያስመሰከረ የሪያል ማድሪድ የወጣቶች አካዳሚ ውጤት መሆኑ ይታወቃል።