ዴንማርካውያን የአሜሪካዋን ካሊፎርኒያ ለመግዛት ዘመቻ ጀመሩ
ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች እስካሁን ፊርማቸውን ያኖሩበት ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ዴንማርካዊ 18 ሺህ ዶላር እንዲያዋጣ ተጠይቋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/273-135837-l-0x42wh-786x458z-1_700x400.jpeg)
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዴንማርክ ስር ያለችውን ግሪንላንድ ለመጠቅለል ማቀዳቸውን መናገራቸው ይታወሳል
ዴንማርካውያን ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የአሜሪካዋን ግዛት ካሊፎርኒያ ለመግዛት የኦንላይን ዘመቻ ጀምረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዴንማርክ ግዛት ስር ያለችውን ግሪንላንድ ለመግዛት ያቀረቡት ሃሳብን ተከትሎ ነው ዘመቻው የተጀመረው።
ዴይሊሜል እንደዘገበው ሃቪየር ዱቶይት በተባለ ግለሰብ የተጀመረው ዘመቻ በጥቂት ስአታት ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎችን ፊርማ አሰባስቧል።
ካሊፎርኒያን "ኒው ዴንማርክ" የሚል ስያሜ እንሰጣታለን የሚሉት የዘመቻው አስተባባሪዎች፥ እያንዳንዱ ዴንማርካዊ 200 ሺህ ክሮነር (18 ሺህ ዶላር) ቢያዋጣ ግዛቷን መግዛት እንችላልን ብለዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብሮች በትሪሊየን ዶላሮች ተሰብስቦ ግዛቷን በመግዛት የዴንማርክን እሴቶች ለማስረጽና ከሞቃታማው የአየር ሁኔታዋም ለመጠቀም የተጀመረው ዘመቻ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው።
ዴንማርካውያን ሃሳቡን እንዲደግፉት የሚወዱትን ነገር አንስተዋል፤ "በካሊፎርኒያ አቮካዶ በብዛት አለ፤ ስለዚህ የአቮካዶ ጭማቂ እንዳሻችሁ ትጠጣላችሁ፤ የአየር ሁኔታውንም ትወዱታለችሁ" ብለዋል።
የካሊፎርኒያ ግዛት ነዋሪዎችን ለማማለልም ዮጋን ጨምሮ የዳኒሾች መገለጫ የሆኑ ምግቦችና ባህላዊ እሴቶችን እንደሚያመጡ የዘመቻው አስተባባሪዎች ተናግረዋል።
"ሌጎ" የተሰኘው የዴንማርክ ታዋቂ ኩባንያ ዴንማርክ ካሊፎርኒያን ለመግዛት ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ድርድር እንዲመራ ሃሳብ መቅረቡ ነው የተነገረው።
ዘመቻው እውን ይሆናል የሚለው አጠራጣሪ ቢሆንም የስላቅ መልዕክቱ ግን በፍጥነት ተደራሽ ሆኗል።
ትራምፕ የዴንማርክ ሉአላዊ ግዛት አካል የሆነችውን ራስ ገዝ አስተዳደር በቁጥጥር ስር ለመዋል በተደጋጋሚ ዝተዋል።
ስትራቴጂካዊ ፋይዳዋ ከፍ ያለውንና በማዕድን ሃብት የበለጸገችውን ግሪንላንድ ለመያዝ ወታደራዊ ሃይልም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደማያደርጉ እስካሁን በግልጽ አልተናገሩም።
የዴንማርክ ምክርቤት አባሉ አንድሬስ ቪስቴንሰን ግሪንላንድ ለ800 አመታት የሀገሪቱ አካል መሆኗን ጠቅሰው ለሽያጭ እንደማትቀርብ ገልጸዋል። አቋማቸውን ለማስረገጥም "በሚገባህ ቋንቋ እነግርሃለው፤ ሚስተር ትራምፕ ገሃነም መውረድ ትችላለህ" ማለታቸውንም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የግሪንላንድ እና ዴንማርክ ግንኙነት
ትራምፕ በግሪንላንድ ባለቤትነት ዙሪያ ዴንማርክ የምታነሳው ሃሳብ ህጋዊነት ላይ የሰጡት አወዛጋቢ አስተያየት መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። "ማንም ዴንማርክ ስለምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ ህጋዊነት አያውቅም፤ ትክክለኛ ባለቤት ቢሆኑ እንኳን ሊተውልን ይገባል፤ (ግሪንላንድ) ለኛ ብሄራዊ ደህንነት ታስፈልገናለች" ነበር ያሉት።
በመልካምድራዊ አቀማመጧ በሰሜን አሜሪካ የምትገኘው ግሪንላንድ ፖለቲካዊ ቁርኝቷ ግን ከአውሮፓ ጋር ነው። ከ9ኛው ክፍለዘመን አንስቶ ከዴንማርክ እና ኖርዌይ ጋር ትስስር አላት። "ኢንዩት" የተባሉ ህዝቦች ከ800 አመት በፊት የሰፈሩባት ግሪንላንድ በ1721 በዴንማርክ ቅኝ ግዛት ውስጥ ገብታለች። በ1953ትም በዴንማርክ ስር ያለች ራስ ገዝ አስተዳደር ሆናለች።
ዴንማርክ አሁንም ድረስ የግሪንላንድን የውጭ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ትቆጣጠራለች።
አሜሪካ በበኩሏ ሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓን በአጭር ርቀት በምታስተሳስረው ግሪንላንድ ወታደራዊ የጦር ሰፈር አላት።
ደሴቷ እንደ ዩራኒየም ያሉ ውድ የተፈጥሮ ሃብቶች መያዟም ይነገራል።