የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ግሪንላንድን ሊጎበኙ ነው
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል
በዴንማርክ ስር ያለችው ግሪንላንድ አውሮፓን እና ሰሜን አሜሪካንን የምታዋስን ቁልፍ ሀገር ነች
የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ግሪንላንድን ሊጎበኙ ነው፡፡
ከሁለት ወር በፊት በተካሄደ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን የመግዛት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
ሁለቱ አህጉራት አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካንን የምታዋስነው ግሪንላንድ በዴንማርክ ስር የምትተዳደር ሀገር ነች፡፡
ይህች ራስ ገዝ በራሷ ጠቅላይ ሚኒስትር የምትመራ ሲሆን በዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን የእንግዛችሁ ጥያቄ ግሪንላንድ ለሽያጭ አትቀርብም ስትል ውድቅ አድርጋለች፡፡
የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትለው ዴንማርክ በበኩሏ ከዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ማግስት የግሪንላንድን ወታደራዊ ዝግጁነት አጠናክራለች፡፡
ከ160 ዓመት በፊት አንድሪው ጆንሰን የተሰኙት ፕሬዝዳንት ግሪንላንድን ለመግዛት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ሁሉ የዶናልድ ትራምፕ አወዛጋቢ ንግግር በኋላ የበኩር ልጃቸው የሆኑት ኤሪክ ትራምፕ ግሪንላንድን ሊጎበኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኤሪክ ጉብኝት የግል እቅድ ነው የተባለ ሲሆን ጉብኝቱም ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ የኤሪክ ትራምፕ የግሪንላንድ ጉብኝት የአሜሪካ መንግስት ይፋዊ ጉብኝት እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡
ግሪንላንድ ባላት መልክዓ ምድራዊ ውበት ተወዳጅ ቦታ ስትሆን የአሜሪካ ሳተላይቶች መረጃ መቀበያ ማዕከላት ቁልፍ ስፍራ ሆናም በማገልገል ላይ ናት፡፡