ትራምፕ ግሪንላንድ ለመቆጣጠር መፈለጋቸውን ተከትሎ ዴንማርክ የቅኝት መርከቦችን ለማሰማራት አቀደች
ዴንማርክ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ በረጅም ርቀት ድኖን የሚደረገውን የቅኝት እና የስለላ ስራ ለማጠናከር 400 ሚሊዮን ዶላር መድባለች ተብሏል
ትራምፕ ከግሪንላንድ በተጨማሪ የፓናማ ቦይን እንደሚጠቀልሉ እንዲሁም ካናዳ የአሜሪካ 51 ግዛት እንድትሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል
ትራምፕ ግሪንላንድ ለመቆጣጠር መፈለጋቸውን ተከትሎ ዴንማርክ የቅኝት መርከቦችን ለማሰማራት አቀደች።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን መቆጣጠር እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን ተከትሎ ዴንማርክ በግሪንላንድ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ለማጠናከር ሁለት የአርክቲክ የቁጥጥር መርከቦችን ለመግዛት እና ቅኝት ለማጠናከር ማቀዷን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ መንግስት በምዕራብ ግሪንላንድ የሚገኘውን የቀድሞ የአሜሪካ የጦር ሰፈር የነበረውን ኤየርፖርት ኤፍ-35 ጄቶችን እንዲይዝ ለማደስም አስቧል።
ዴንማርክ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ በረጅም ርቀት ድኖን የሚደረገውን የቅኝት እና የስለላ ስራ ለማጠናከር 400 ሚሊዮን ዶላር መድባለች ተብሏል።
ትራምፕ በከፊል ራስ ገዝ የሆነችውን የዴንማርኳን የአርክቲክ ግዛት ግሪንላንድን ለመያዝ ያላቸውን ፍላጎት በድጋሚ በዚህ ሳምንት ገልጸዋል። የግሪንላንድ መከላከያ እና ጸጥታ ሁኔታዎች የምትቆጣጠረው ዴንማርክ በሰፊዋ ደሴት ያላት ወታደራዊ አቅም ውስን ነው።
በአሁኑ ወቅት አራት ያረጁ የቁጥጥር መርከቦች፣ አንድ የቅኝት አውሮፕላን እና 12 ዶግስሌጂ ቃኝዎች ያሉ ሲሆን የፈረንሳይን አራት እጥፍ የምታክለውን ደሴት እንዲቆጣጠሩ ተመድበዋል።
ዴንማርክ የመከላከያ በጀቷን በእጁጉ ከቀነሰች ከእስር አመታት በላይ በኋላ ባለፈው አመት ለ 10 አመታት የሚያገለግል የ 26 ቢሊዮን ዶላር የመደበች ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተወሰነው ለአርክቲክ የሚውል ነው።
ባለፈው ሳምንት የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላርስ ሎክ ራስሙሰን ዴንማርክ ግዙፍ ወታደራዊ ግንባታ እያደረገች መሆኑን ለትራምፕ ለማሳወቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ነገርግን የመከላከያ ሚኒስትሩ ትሮልስ ለንድ አስፈላጊ ወታደራዊ ኢንቨስትመንቶች ለበርካታ አመታት ችላ ተብለው መቆየታቸውን በትናንትናው እለት ገልጸዋል።
ዴንማርክ በግሪንላንድ የምታደርገው ወታደራዊ ግንባታ የአሜሪካን ስጋት የሚቀርፍ እንዲሆን ይደረጋል የሚል አቋም እያራመደች ነው።
አሜሪካ አሁንም በሰሜንምዕራብ ግሪንላንድ ፒቱፊክ ወታደራዊ ይዞታ አላት።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከግሪንላንድ በተጨማሪ የፓናማ ቦይን እንደሚጠቀልሉ እንዲሁም ካናዳ የአሜሪካ 51 ግዛት እንድትሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።