ጠቅላይ ሚንስትሩ ሩሲያን በመደገፍ ይታወቃሉ
የስሎቫኪያ ጠቅላይ ሚንስትር በጥይት ተመተው ሆስፒታል ገቡ።
ባሳለፍነው ጥቅምት በተደረገ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡት የስሎቫኪያ ጠቅላይ ሚንስትር በጥይት ተመተው ሆስፒታል ገብተዋል ተብሏል።
ሮይተርስ የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚንስትር ሮበርት ፊኮ የካቢኔ ስብሰባ አድርገው ሲወጡ ከአንድ ግለሰብ በተተኮሰ ጥይት ተመተዋል።
ፖሊስ ተጠርጣሪውን ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር አውሎታል የተባለ ሲሆን በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ ምርመራ በመካሄድ ላይ እንደሆነም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል የተባለ ሲሆን የሀገሪቱ መንግሥት እስካሁን ስለ ጉዳዩ በይፋ ያለው ነገር የለም።
ጠቅላይ ሚንስትር ፊኮ ኔቶን ጨምሮ ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረግ የለባቸውም በሚል አቋማቸውም ይታወቃሉ።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ያለው ጦርነት እንዲቆም ከተፈለገ ኪቭ ክሪሚያ የሩሲያ መሆኗን ማመን እና መቀበል እንዳለባት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።