በዳርፉር ባለፉት 18 ዓመታት ውስጥ በተፈጠረ ግጭት 300 ሺህ ዜጎች ተገድለዋል
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት ሰባት ሰዎች ሲሞቱ 16 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተዘግቧል፡፡
በደቡባዊ ዳርፉር ግዛት የታጠቁ ሰዎች አደረሱት በተባለ ጥቃት የሰባት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 16 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል።
አደጋው ከደረሰ በኋላም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።በጃንጃዊድ ሚሊሻዎች ደረሰ በተባለው በዚህ ጥቃት ከ200 በላይ ታጣቂዎች አደጋውን እንዳደረሱትም ዘገባው አክሏል።
ጥቃቱን ለማስቆምም የጸጥታ ሀይሎች ወደ ቦታው አቅንተው ህብረተሰቡን በማረጋጋት ላይ ቢሆኑም ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንደለቀቁም ተገልጿል።
በፈረንጅቹ 2003 ዓመት አንስቶ በዳርፉር በተከሰተ የጎሳ ግጭት 300 ሺህ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
ይሄንን አደጋ ለማስቆምም የተመድ-አፍሪካ የተቀናጀ ዘመቻ ሰላም የማስከበር ስራ ፕሮግራም ሲተገር የቆየ ሲሆን ከ16 ሺህ በላይ ሰላም አስከባሪ ጦር በስፍራው ተሰማርቶ ነበር።ይሁንና ይህ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ካሳለፍነው ታህሳስ ወር ጀምሮ እንዲቆም ድርጅቱ ውሳኔ ቢያሳልፍም በዳርፉር አሁንም ዜጎች በሚሊሻዎች ሲገደሉ እና ሲፈናቀሉ ይታያል።
ሱዳንን ለ30 አመታት ሲያስተዳድሩት የነበሩትና ከ3 አመት በፊት በተነሳባቸው ህዝባዊ አመጽ ከስልጣን የተነሱት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ኦማር አልበሽር የዘር ማጥፋት ወንጅል ፈጽመዋል ተብለው ተወንጅለዋል፡፡ አሁን በሱዳን በእስር ላይ የሚገኙት አልበሽር ጉዳያቸው በአለምአቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት እንዲታይ ተላልፈው ሊሰጡ መሆኑም ተሰምቷል፡፡