የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
ማልታዊቷ ፖለቲከኛ ሚጾላ ቴዴስኮ ሳሶሊን ተክታ ህብረቱን በፕሬዝዳንትነት እንደምትመራም ህብረቱ አስታውቋል
የቀድሞው የቴሌቪዥን ዜና አንባቢ ዴቪድ ሳሶሊ በ65 ዓመታቸው ዛሬ ጠዋት ማረፋቸው ተነግሯል
የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ሳሶሊ በ65 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ቃል አቀባያቸው አስታወቁ፡፡
ጣሊያናዊው የቀድሞ ጋዜጠኛ እና የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ከሁለት ሳምንት በላይ ለሚሆን ጊዜ በጠና ታመው ነበር ተብሏል፡፡
ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ሁሉንም መደበኛ እንቅስቃሴዎች ሰርዘው ነበር የተባለላቸው ሳሶሊ ያጋጠማቸውን ህመም ለመቋቋም ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ ሆስፒታል ገብተው እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ቃል አቀባያቸው ሮቤርቶ ኩይሎ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ሳሶሊ ህመማቸው በርትቶ ዛሬ ጠዋት አርፈዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በፕሬዝዳንቱ ሞት ማዘኑን ገልጿል፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደር ለየን “ታላቅ አውሮፓዊ እና ኩሩ ጣሊያናዊ” ባሉት በሳሶሊ ሞት ማዘናቸውን ገልጸው “ምርጥ ጋዜጠኛ፣ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት እና ከሁሉም በላይ ውድ ጓደኛ ነበር” ብለዋል፡፡
የቀድሞው የቴሌቪዥን ዜና አንባቢ 705 መቀመጫዎች ያሉትንና ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በአባልነት የተቀላቀሉትን የአውሮፓ ፓርላማን በፕሬዝዳንት መምራት የጀመሩት ከ2019 ጀምሮ ነበር፡፡
የሳሶሊ የፕሬዝዳንትነት ዘመን በዚህ በያዝነው የታህሳስ ወር ነበር የሚያበቃው፡፡ ሆኖም በኋላፊነቱ የመቀጠል ፍላጎት አልነበራቸውም ተብሏል፡፡
ማልታዊቷ ፖለቲከኛ ሚጾላ ቴዴስኮ ሳሶሊን ተክታ ህብረቱን በፕሬዝዳንትነት እንደምትመራም ህብረቱ አስታውቋል፡፡