የቱርክና የጀርመን መሪዎች አንካራ፤ የአውሮፓ ሕብረትን ለመቀላቀል በጀመረችው ሂደት ላይ እየተወያዩ ነው
አንጌላ ሜርክል እና ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን በእስታንቡል ውይይት እያደረጉ ነው
ሁለቱ መሪዎች የጋራ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል
የቱርክ እና የጀርመን መሪዎች አንካራ፤ የአውሮፓ ሕብረትን ለመቀላቀል በጀመረችው ሂደት ላይ በእስታንቡል ውይይት እያደረጉ መሆናቸውን አስታወቁ።
የስልጣን ጊዜያቸው ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ የቀራቸው የጀርመኗ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በቱርክ እስታንቡል ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸውን የቱርክ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስታውቋል።
መራሄተ መንግስቷ በፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን አቀባበል እንደተረገላቸው የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
ሁለቱ ወገኖች ቱርክ፤ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገር ለመሆን የጀመረችውን ሂደት በተመለከተ እንደሚወያዩ ይጠበቃል ተብሏል።
መሪዎቹ ፤ በአንካራ እና በበርሊን የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ሀገራቱ ያላቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት እየተካረረ የመጣ መሆኑም ይጠቀሳል።
የጀርመን እና የቱርክ መሪዎች ሰፋ ባለመልኩ ይወያያሉ ተብሎ የሚጠበቀው ደግሞ በስደተኞች ጉዳይ እንደሆነም የጀርመን ድምጽ በዘገባው አካቷል።
ስደተኞችን በተመለከተም ታሊባን እያስተዳደራት ያለችው አፍጋኒስታን የአንጌላ ሜርክል እና የረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን ሌላኛዋ የመወያያ ጉዳይ ትሆናለች ተብሏል።
አሁን ላይ ቱርክ ከሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ከሶሪያ እና ከአፍጋኒስታን ተቀብላ እያስተናገደች ነው።ይህም አንካራ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በገባችው ውል መሰረት እየተካሄደ ያለ ሲሆን የመሪዎቹ ዋነኛ የመወያያ ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የአውሮፓ ሕብረት ዘዋሪ እየተባሉ የሚጠሩት ሜርክል ስደተኞችን በሚመለከት ከአቻቸው ኤርዶሃን ጋር ያደረጉት ውይይት ምንድነው የሚለው በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደሚታወቅ ተገምቷል።
ቱርክ አሁን ከያዘችው ስደተኛ ባለፈም ከአፍጋኒስታን በርካቶች ሊገቡባት እንደሚች ተገምቷል። የአውሮፓ ሕብረት ታሊባንን አምልጠው ወደ ቱርክ የሚገቡ ስደተኞችን ለመርዳት ለአንካራ ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር መስጠት እንደሚፈልግ ተዘግቧል።
ይሁንና የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጠኢብ ኤርዶሃን ሀገራቸው ከዚህ በላይ ስደተኞችን መቀበል የለባትም ሲሉ በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል። ሁለቱ መሪዎች ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ የጋራ መግለጫ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።