አትሌት ዳዊት ስዩም በ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዘገበች
በወንዶች በተካሄደው ውድድር አትሌት በሪሁ አረጋዊ 1ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል
በወንዶች በ10 ኪሎ ሜትር ውድድርም አትሌት ጭምዴሳ ደበላ አሸንፏል
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዳዊት ስዩም በፈረንሳይ ሊል በተካሄደ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስዘመገበች።
አትሌት ዳዊት ስዩም ርቀቱን 14 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ የገባች ሲሆን፤ ከዚህ ደቀም በርቀቱ ተይዞ የነበረውን 14 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በሁለት ሰከንድ በማሻሻል ነው ክብረወሰኑን በእጇ ያስገባችው።
አትሌት ዳዊት ስዩም በርቀቱ ያስመዘገበችው አዲስ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን ሆኖ መጽደቅ እየተጠባበቀ መሆኑን የዓለም አትሌትኪስ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
በርቀቱ ኬንያዊቷ ኖራህ ጁቴሩ 14 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት 2ኛ ደረጃን ስትይዝ፤ ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ማሞ 14 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በሆነ ሰዓት 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።
በወንዶች በተካሄደው የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ደግሞ አትሌት በሪሁ አረጋዊ 12 ደቂቃ ከ52 በሆነ ሰዓት በመግባት 1ኛ ደረጃን ይዞ በበላይነት አጠናቋል።
ኡጋንዳዊው ሆሴያ ኪፕላንጋት 2ኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ያሲን ሀጂ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቅ ችሏል።
በሌላ ውድድር በ10 ኪሎ ሜትር የወንዶች የጎዳና ላይ ሩጫ ኢትዮጵያዊው አትሌት ጭምዴሳ ደበላ 27 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ውድድሩን በአንደኛነት አጠናቋል።