በማሊ ዋና ከተማ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 70 ሰዎች ተገደሉ
ታጣቂዎቹ ከማክሰኞ ጀምሮ በፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም እና በአየር መንገድ ላይ ነው ጥቃት የፈጸሙት
የማሊ ወታደራዊ አስተዳደር የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ወታደሮችን ከሀገር እንዲወጡ ካደረገ በኋላ ፊቱን ወደ ሩስያ አዙሯል
በማሊ ዋና ከተማ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ሳምንት በፈጸሟቸው ጥቃቶች 70 ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡
ላለፉት አስርተ አመታት በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የሽብር ጥቃቶች ጉዳት እያስተናገደች የምትገኝው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በዚህ ሳምንትም መጠኑ ከፍ ያለ ጥቃት ደርሶባታል፡፡
በዋና ከተማዋ ባማኮ ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም እና የሀገሪቱ አየር መንገድ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡
ታጣቂ ቡድኖቹ ይህን ጥቃት የፈጸሙት በማዕከላዊ የሀገሪቷ ክፍል ጭምር የትኛውንም አይነት የሽብር ተልዕኮ ማሳካት እንደሚችሉ ለማሳየት ነው ተብሏል፡፡
የሀገሪቱን መንግሰት በመፈንቅለ መንግስት አስወግዶ እየመራ የሚገኝው ወታደራዊ አስተዳደር በማሊ የሚገኝው የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳይ እየተሻሻለ እንደሚገኝ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡
ወታደራዊ አስተዳደሩ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ወታደሮችን ከሀገር እንዲወጡ ካደረገ በኋላ ፊቱን ወደ ሩስያ አዙሯል፡፡
ሽብርተኞችን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሩስያ ቅጥር ወታደር ቡድን ዋግነር ባሳለፍነው ሀምሌ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮቹ በማሊ እንደተገደሉበት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ የተከሰተውን ጥቃት ተከትሎ አስተዳደሩ የሟቾችን ቁጥር ይፋ ባያደርግም ሮይተርስ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች አገኝሁት ባለው መረጃ ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ዘግቧል፡፡
ማሊ፤ ፈረንሳይ የአየር ክልሌን በመጣስ ታጣቂዎችን እየደገፈች ነው ስትል ከሰሰች
በጥቃቱ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች በሆስፒታል የህክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የማሊ ጋዜጦች በበኩላቸው በጥቃቱ የተገደሉ 50 የፖሊስ ሰልጣኞች ስርአተ ቀብር በትላንትናው እለት መፈጸሙን ዘግበዋል፡፡
የማሊ ወታደራዊ አስተዳደር ከታጣቂዎች እና ሽብርተኞች ጋር በገባበት ውግያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ሚሊየኖች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡