ሶማሊያ የኢትዮጵያ አማጺያንን ልታስታጥቅ እንደምትችል አስጠነቀቀች
በታሪክ ሁለት ጊዜ ይፋዊ ጦርነት ያደረጉት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አማጺያንን የማስታጠቅ ልምድ አላቸው
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የወደብ ስምምነት ከተገበረች ሶማሊያ በኢትዮጵያ ያሉ ታጣቂዎችን እደግፋለሁ ብላለች
ሶማሊያ የኢትዮጵያ አማጺያንን ልታስታጥቅ እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ካደረገች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ሻክሯል፡፡
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞዓሊም ፊኪ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ከተገበረች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ታጣቂዎች ልንደግፍ እንችላለን ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “ስምምነቱ ከተተገበረ ታጣቂዎችን አልያም የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል የሚታገሉ አማጺያን ጋር ለመገናኘት እንሞክራለን” ብለዋል፡፡
“እስካሁን ታጣቂዎቹን ለማግኘት እየሞከርን አይደለም፣ ለችግሩ ሁሉ መፍትሄ ሊኖር እንደሚችል ተስፋ አለን” የሚሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ወደ መተግበር ከገባች ግን አማጺያኑን መርዳት የምችልበት መንገድ ይኖራል ሲሉ መናገራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ህወሃትን ትረዱ ነበር? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ተመካክረንበት ነበር፣ ነገር ግን እኛ ለሶማሊያ ፍላጎት ስንል ኢትዮጵያ እንድትበታተን አንፈልግም፣ ነገር ግን እነሱ ሶማሊያን ለመጉዳት ከገፉበት እኛም አማጺያንን ለመርዳት አማራጭ አለን“ ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ዙሪያ የአሜሪካ አቋም ምንድን ነው?
በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና አፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ምክትል ተጠሪ የሆኑት አምባሳደር ነብዩ ተድላ በኤክስ አካውንታቸው ላይ የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስተያየትን ተችተዋል፡፡
አምባሳደር ነብዩ በምላሻቸው ከሞቃዲሾ አቅራቢያ ውጪ ያሉ ቦታዎችን ማስተዳደር የማይችሉት የሶማሊያ ባለስልጣናት የአልሻባብ ተወካይ ሆነው መቅረባቸው ያስቃል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
የሶማሊያ እንቅስቀሴ ኢትዮጵያ ለዓመታት ያደረገችላትን ድካም እና ልፋት መና የሚያስቀር ነው ሲሉም የሚኒስትሩን አስተያየት ተችተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በታሪክ ሁለት ጊዜ ይፋዊ ጦርነት ያደረጉ ሲሆን በ1980ዎቹ እና 70ዎቹ ላይ አንዳቸው የሌላኛውን አማጺ ይረዱም ነበር ተብሏል፡፡
የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡበትን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡