ቱርክ የሶማሊያን የባህር ክልል ለመጠበቅ በቀጣዩ ወር የጦር መርከቦቿን ልትልክ ነው
የአንካራ የባህር ሃይል በአካባቢው ነዳጅ ፍለጋ ላይ ለሚሰማራ ኩባንያ ተጨማሪ ጥበቃ ያደርጋል ተብሏል
ቱርክ በመዲናዋ አንካራ በ6 ሚሊየን ዶላር ለሶማሊያ ኤምባሲ ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗ ተገልጿል
ቱርክ የሶማሊያን የባህር ክልል ከውጭ ከሚሰነዘር ስጋት ለመከላከል በመጪው ወር የጦር መርከቦቿን በአካባቢው ልታሰማራ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ አመት መጀመርያ የመከላከያ ስምምነትን የተፈራረሙት ሞቃዲሾ እና አንካራ በሁለትዮሽ እና የደህንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡
ቱርክ በቀጣዩ ወር በሶማሊያ የባህር ክልል ታሰማረዋለች የተባለው የባህር ሀይልም የዚህ የመከላከያ ስምምነት አንድ አካል ነው፡፡
ወደ ቀጠናው የሚመጡት ሁለት አይነት መርከቦች ሲሆኑ አንድኛው አንካራ በአካባቢው ለምታደርገው የነዳጅ ማውጣት እንቅስቃሴ የሚያግዝ ሲሆን ሌሎቹ ድግሞ የሶማሊያን የባህር ክልል እና የነዳጅ አውጭ ቡድኑን የሚጠብቁ ናቸው ተብሏል፡፡
የቱርክ የኢነርጂ ሚንስትር አልፓረሰላን ቤራክታር ባሳለፍነው ሳምንት ለሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን እንደተናገሩት ተርኪሽ ፔትሮሊየም የተባለው ኩባንያ እያንዳንዳቸው 5 ሺህ ኪሎሜተር ስኩየር በሚሸፍኑ ሶስት አካባቢዎች ላይ የነዳጅ ፍለጋ እንዲያደርግ ከሶማሊያ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡
ሀገራቱ በገቡት ስምምነት መሰረትም እንደሚገኘው የነዳጅ መጠን ለመከፋፈል እና ላስፈለጋቸው አካል መሸጥ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡
ይህን ተከትሎም ሁለት መካከለኛ የውግያ መርከቦች እና ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ አጋዥ መርከቦች አካባቢውን ለመቃኘት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ሚድልኢስት አይ ዘግቧል፡፡
ከጥቅምት ወር ጀምሮ እንደሚሰማሩ የተነገረላቸው እነዚህ መርከቦች ከባህር ላይ ሽፍቶች እንዲሁም ከምድር ሊሰነዘር የሚችል የትኛውንም ጥቃት የመመከት እና የቅኝት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መፈጸም የሚያስችል አቅም ያላቸው ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
ከሶማሊያ ጋር ትብብሯን እያጠናከረች የምትገኘው ቱርክ በመዲናዋ አንካራ በ6 ሚሊየን ዶላር ለሶማሊያ ኤምባሲ ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗም ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በወደብ ጉዳይ የተፈራረመችውን የመግባብያ ስምምነት ተከትሎ ሞቃዲሾ እና አንካራ የመከላከያ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ስምምነት ፈጽመዋል፡፡
አንካራ በሶማሊላንዱ ወደብ ምክንያት ቅራኔ ውስጥ የሚገኙትን አዲስአበባ እና ሞቃዲሾ ለማሸማገል ሁለት ያልተሳኩ ጥረቶችን ማድረጓ የሚታወስ ነው።