የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር የግድያ ዛቻ ደረሳቸው
የግድያ ዛቻውን የሰነዘረው ወጣት ስራ ያልያዘና ከመንግስት የሚያገኘው ገቢ ይቀንሳል መባሉ ያበሳጨው ነው ተብሏል
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጋ ሜሎኒ እና ሴት ልጃቸው የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል ተባለ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በኢንተርኔት ነው ከአንድ ስራ ፈላጊ ወጣቱ የግድያ ደብዳቤ የደረሳቸው።
ግራ ዘመሙ የሜሎኒ መንግስት ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ለዜጎች የሚከፈል ገንዘብን ለመቀነስ፤ በ2024 ደግሞ ሙሉ በሙሉ የማቆም ውጥን ይዟል።
በህዳር ወር 2022 ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር የመስራት አቅም ያላቸው ወጣቶች ጭምር የድጎማ ገንዘብ መውሰዳቸውን ይቃወማሉ።
ሀገራቸው በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ወድቃ ይህ ያልተገባ ክፍያ መቀጠል እንደሌለበትም ደጋግመው ገልጸዋል።
ይህ ያበሳጨው የ27 አመት የሲሲሊ ወጣትም ለጠቅላይ ሚኒስትሯ እና ሴት ልጃቸው በኢንተርኔት የግድያ ዛቻውን መላኩ ተሰምቷል።
የግድያ ዛቻው ለኑሮዬ መሰረታዊ የሆነውን ክፍያ ካቋራጥሽው እኔም የአንቺን (የጠቅላይ ሚኒስትሯን) እና ልጅሽን እስትንፋስ አቋርጠዋለው የሚል ይዘት አለው።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ፥ ወጣቱ በጥላቻ የተሞሉ ቃላትን ተጠቅሞ የላከው የግድያ ዛቻ የሚረብሽ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስት ስራዎችን በዛቻና አመጽ ተጽዕኖ ውስጥ ለመክተት ማሰብ ግን ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን በመግለጽ ጣሊያናውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ድርጊቱን እንዲያወግዙት ጠይቀዋል።
የሀገሪቱ ፖሊሲ በኢንተርኔት ጠቅላይ ሚኒስትሯን እና ልጃቸውን ለመግደል የዛተውን ሰው በቁጥጥር ስር አውላለሁ ብሏል።
የጣሊያን መገናኛ ብዙሃን ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ስለመያዙ እየዘገቡ ነው።
ቤቱ ሲፈተሽ የግድያ ዛቻውን የላከበት ኮምፒውተር ስለመገኘቱና የትዊተር አካውንቱ ተዘግቶ ምርመራው መቀጠሉንም ተገልጿል።