የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተረፉ
ጠ/ሚኒስትር ዴቢባህ በተሸከርካሪያቸው በመጓዝ ላይ እያሉ ነው ድንገት በተከፈተ ተኩስ ጥቃቱ የተፈፀመባቸው
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተደረገው ሙከራ የሊቢያን የፖለቲካ ውጥረት እንዳያባብሰው ተስግቷል
የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ አል ዴቢባህ ከግድያ ሙከራ መትረፋቸው ተገለፀ።
የግድያ ሙከራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቤታቸው በማቅናት ላይ እያሉ በድንገት በተከፈተ ተኩስ መፈፀሙን ነው ሮይተርስ የአይን እማኞቹን ዋቢ አድርጎ የዘገበው።
ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቢባህ ምን አይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው መትረፋቸው ነው የተገለፀው።
በጠቅላይ ሚኒሰትሩ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የግድያ ሙከራ ስለመሆኑ አያጠራጥርም የተባለ ሲሆን፤ ጥቃቱን ያደረሱት እነማን ናቸው የሚለው ላይ ምርመራ እንደሚደረግም ተነግሯል።
የአካባቢው መገናኛ ብዙሃ ባወጡት ምስል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቢባህ ሲጓዙበት የነበረው ተሸከርካሪ የፊት ለፊት መስታወት፣ መብራት እንዲሁም በጎን በኩል በጥይት መመታቱን ያመለክታል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዴቢባህ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የግድያ ሙከራ መሆኑ ከተረጋገጠ በሊቢያ ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ሊያባብስ ይችላል በሚል ተስግቷል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሊቢያ ያሉ ታጣቂ ኃይሎች በርካታ ተዋጊዎቻቸውን እና መሳሪያዎችን ወደ ሀገሪቱ ዋና ከተማ ትሪፖሊ እያስጠጉ መሆኑን ተከትሎ የፖለቲካ ውጥረቱን አባብሶታል።
አብዱልሃሚድ አል ዴቢባህ ባሳለፍነው ዓመት ነበር የሊቢያ ብሄራዊ አንድነትን በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ በተመድ አጋዥነት የተሸሙት።