አብዲሰዒድ ሙሴ አሊ ሙከራውን ፖለቲካዊ ነው ብለውታል
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሰዒድ ሙሴ አሊ ከተቀጣባቸው የግድያ ሙከራ ተረፉ፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሃሙስ ነው ጋልካዮ በተባለው የፑንትላንድ አካባቢ የግድያ ሙከራው የተደረገባቸው፡፡
ጋልካዮ ከሃገሪቱ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በስተ ሰሜን በ750 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
አብዲሰዒድ ሙሴ እና ቤተሰባቸው ከፑንትላንድ አካባቢ ጎሳ መሪዎች መካከል አንዱ በሆኑት በያሲን አብዱሰመድ ቤት በአፍጥር ስነ ስርዓት ላይ ሳሉ ግጭት እንደተቀሰቀሰ ተነግሯል፡፡
በግጭቱ ከሚኒስትሩ አጃቢዎች አንዱ መገደሉንና የጎሳ መሪው እንደተጎዱ የኬንያው ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ግጭቱ በፑንትላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር የጸጥታ አካላት መቀስቀሱን ነው ጋዜጣው የዘገበው፡፡
ሶማሊያ ከ30 ዓመታት በኋላ ሲኒማ ማሳየት ጀመረች
የረመዳን የመጨረሻ የጾም ቀናትን በጋልካዮ ለማሳለፍ በማሰብ ወደ ፑንትላንድ ማቅናታቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሙከራውን ፖለቲካዊ ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ለአፍጥር ወደተጋበዙበት ስፍራ ለመሄድ ቤተሰባቸውን ይዘው ከቤታቸው ሲወጡ ከአራት ጠባቂዎቻቸውና ሁለት አጃቢዎቻቸው ጋር በመሆን እንደነበር የገለጹም ሲሆን ጠባቂዎቻቸው ሙከራውን ማክሸፋቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ከጠባቂዎቻቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው መቁሰሉንና በቤታቸው እንዲያፈጥሩ የጋበዟቸው የጎሳ መሪ ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ግጭትን ፖለቲካዊ ግብን ማሳኪያ የመጨረሻው መንገድ አድርጎ ማሰብን እንደሚያወግዙ ያስታወቁት ሙሴ አሊ በሙከራው የተሳተፉትን ሁሉ በህግ ተጠያቂ አደርጋለሁም ብለዋል፡፡
ሆኖም ሙዱግ የተባለው የራስ ገዝ አስተዳደሩ አካባቢ ገዢ ግጭቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቆስቋሽነት የተቀሰቀሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አብዲሰዒድ ሙሴ አሊ "ስለ ከሸፉ" የመንግስት ፖሊሲዎች ለማውራት ወደ ፑንትላንድ መምጣታቸውንም ነው ገዢው የተናገሩት፡፡
ሆኖም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ህይወታቸውን ለመንጠቅ የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የፑንትላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሰዒድ አብዱላሂ ዴኒ ሶማሊያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ከመሃመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) እየተፎካከሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡