ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ከዜሚ ጉዳት እንዳልደረሰባቸውም ተነግሯል
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ከዜሚ በዛሬው እለት የግድያ ሙከራ እንደተፈፀመባቸው ተነገረ።
የግድያ ሙከራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ላይ በድሮን በተጣለ ቦምብ አማካኝነት የተፈፀመ መሆኑን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም የተባለ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ከዜሚ የሀገሪቱ ህዝብ እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል።
በግድያ ሙከራው የጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ከዜሚ ሁለት ጠባቂዎች ላይ መጠነኛ የመቁሰል አደጋ መድረሱንም ነው ባለስልጣናቱ ያስታወቁት።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተፈፀመውን ሙከራ ተከትሎ የተቋቋመ የጋራ ግብረ ኃይል በሰጠው መግለጫ፤ ጥቃቱ የተፈፀመው በድሮን በተጣለ ቦምብ መሆኑን ጠቅሷል።
በጥቃቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ከዜሚ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ በመጥቀስ፤ በመልካም ጤነንነት ላይ እንደሚገኙም አክሎ ገልጿል።
የገድያ ሙከራው ከወር በፊት በኢራቅ የተደረገውን የፓርላማ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በገባችት ወቅት ነው።