ጥቃቱን “በፈሪ ሽርተኞች የተቃጣ ነው” ያሉት አዲሱ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ድርጊቱን “የግልበጣ ሙከራ” ብለውታል
በየመን ኤደን አየር ማረፊያ በተፈጸመው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 10 ደርሷል ተብሏል፡፡ በእርግጥ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ የሚችል ነው፡፡ በርካቶችም ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
ኤደን በሳዑዲ አረቢያ አዲስ በተዋቀረው መንግስት በጊዜያዊ ዋና ከተማነት ተመርጣ ነበር፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመውም የአዲሱ መንግስት የካቢኔ አባላትን ያሳፈረ አውሮፕላን በከተማይቱ አየር ማረፊያ በደረሰ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ነው፡፡
ከፍተኛ ፍንዳታ እና ቃጠሎ በአየር መንገዱ ማጋጠሙንም የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
ቀድመው የወጡ መረጃዎች በፍንዳታው ምክንያት 5 ሰዎች መሞታቸውን አመልክተው ነበረ፡፡ ሆኖም ቁጥሩ አሁን አሻቅቦ 25 ደርሷል እንደ አረብ ኒውስ ዘገባ፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዒን አብዱልማሊክ ሰዒድ ከነ ካቢኔያቸው ጭምር ደህና መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል፡፡
ሰዒድ ጥቃቱን በየመን መንግስት እና በህዝባችን ላይ በፈሪ ሽርተኞች የተቃጣ ብለውታል፡፡ በግልበጣ ሙከራነትም ነው የጠቀሱት፡፡ ሆኖም ይበልጥ ቢያጠነክረን እንጂ ውጥናችን እስኪሟላ ከቶ አይበግረንም ብለዋል፡፡
ለተጎጂዎች ማዘናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የመረጃ ሚኒስትሩ ሞሃማር አል ኤርያኒም አውግዘዋል፡፡
በሃውቲ የተፈጸመው ጥቃት ሃገራዊ ግዴታችንን ከመወጣት አያስተጓጉለንምም ነው ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
ሆኖም እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን በይፋ የወሰደ አካል የለም፡፡
ጥቃቱ ሲፈጸም በየመን የሳዑዲ አምባሳደር መሃመድ ሰዒድ አል ጃቢር ጭምር ነበሩ፡፡ ሆኖም ባለስልጣናቱ ያለአንዳች ጉዳት ደህንነታቸው በጥብቅ ሊጠበቅ ወደሚችልበት ፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግስት መወሰዳቸውን ነው ሚድልኢስት አይ የዘገበው፡፡
የባህር ዳርቻዋ ከተማ ኤደን መገኛ የሆነው ደቡባዊ የመን የመገንጠል ጥያቄ ያለበት ነው፡፡ ተገንጥለው ሃገር መሆን የሚፈልጉ ቡድኖች በፕሬዝዳንት አብድ ረቡህ መንሱር ሃዲ ከሚመራው መንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል፡፡
ዘንድሮ ራስ ገዝ ነን ሲሉ አውጀው የነበሩ መሆኑም በየመን ምድር ተኩስ እንዲቆም ለሚፈልገው የመንግስታቱ ድርጅት ጭምር አስቸግሮ ነበር፡፡
ከብዙ ድርድሮች በኋላም ተገንጣዩን ቡድን ጨምሮ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የሃዲ መንግስት እና ሌሎችም የፖለቲካ ሃይሎች የተካተቱበት አዲስ ጥምር መንግስት ለመመስረት ከ15 ቀናት በፊት ስምምነት ላይ ደርሰው ነበረ፡፡
አዲሱ ጥምር መንግስት በጸረ ሃውቲ ዘመቻ መሪዋ ሳዑዲ አረቢያ አስተባባሪነት የተቋቋመ ነው፡፡ 24 የካቢኔ አባላት አሉት፡፡ አባላቱ ቃለ መሃላቸውን ባሳለፍነው ቅዳሜ ፈጽመው ነበር ዛሬ ወደ የመን የተመለሱት፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጥቃቱን አውግዛለች፡፡ በምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ በሪያድ የተደረሰውን ስምምነት የጣሰ ስትል ኮንናለች፡፡
የሰላም ውጥኑን የሚያደፈርስ እንደሆነ በመጥቀስም ነው የኮነነችው፡፡