“የግድቡ ጉዳይ ወደ ዲ.አር ኮንጎ የማለፉ ነገር ሊያስጨንቀን አይገባም”- ስለሺ በቀለ
ከዚህ ውጭ ግን ሊሆን የሚችል ነገር እንደሌለ ሚኒስትሩ ተናግረዋል
“በትብብር ማዕቀፉ አስቸጋሪ አንቀጾች ላይ ከስምምነት እንዲደረስ መፍትሄ ያመጣች ሃገር ናት፤ አሁንም ያን እንደምታደርግ እንጠብቃለን”
የግድቡ የድርድር ጉዳይ ከደቡብ አፍሪካ እጅ ወጥቶ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እጅ መግባቱ “ሊያስጨንቀን አይገባም” ሲሉ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ የግድቡን የግንባታ እና የድርድር ሂደቱን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ዲ.አር ኮንጎ የተፋሰሱ (ናይል) ሃገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ውስጥ (በተፋሰሱ ሃገራት መካከል ያለውን ችግር ግድቡን ጨምሮ) በደንብ እንደምትረዳ ገልጸዋል፡፡
ከሰሞኑ መግለጫዎችን ሰጥታለች በሚል በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች የተነገሩ ነገሮች ነበሩ፡፡
ሆኖም “የእኛ አካሄድ (መርህ) ከዚያ ጋር አይደለም” ነው ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
የማንኛውንም አባል ሃገር መብት ሳትጋፋ እና ሳታዳላ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያሉትን እና የሚኖሩትን ነገሮች ታቀላጥፋለች ተብሎ ይታሰባል ያሉም ሲሆን ልክ ደቡብ አፍሪካ ሁሉ ከፍተኛ ጥረትን ታደርጋለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
በተፋሰሱ ሃገራት የትብብር ማዕቀፍ (CFA) በነበሩ አስቸጋሪ አንቀጾች ላይ መፍትሄ ያመጣች እና ሃገራቱ እንዲስማማ ያደረገች ሃገር መሆኗንም ነው ስለሺ የተናገሩት፡፡
አሁንም ያን እንደምታደርግ እና መፍትሄ እንደምታመጣ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
ዲ.አር ኮንጎ በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነትን ከደቡብ አፍሪካ ትረከባለች፡፡
ይህ የህብረቱን አባል ሃገራት የበለጠ የሚያቀራርብ ስራ ለመስራት እንደሚስችላት ቢታሰብም ከግብጽ ጋር ያላት ቀረቤታ በግድቡ የሶስትዮሽ የውይይት እና የድርድር ሂደት ላይ ጥላ እንዳያጠላ የሚል ስጋት በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተንጸባርቋል፡፡
ቀጣይ የህብረቱ ሊቀመንበር መሆኗ በድርድሩ ሂደት በአሉታ እና በአዎንታ ሊገለጽ የሚችል ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ይኖረው ይሆን? ከደቡብ አፍሪካ የተሻለ ሚናን በገለልተኝነት ትጫወትስ ይሆን የሚል ጥያቄን ሲያነሱ የሚደመጡም አልታጡም፡፡
ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ግን ሃገራቱን አቀራርቦ ለመፍትሄ ከማብቃት ውጭ ሊሆን የሚችል ነገር የለም ሲሉ በመግለጫው ተናግረዋል፡፡
“ጥበብ የተሞላበት እና ሚዛናዊ የሆነ ነገርን እንደሚሰሩ ነው የምንጠብቀው እንጂ ለአን አድልተው ሌላውን የሚጫኑ ከሆነ የሚሆን ነገር አይደለም” ሲሉም ነው በአጭሩ ያስቀመጡት፡፡
ኢትዮጵያ ከዲ.አር ኮንጎ ጋር የቆየ ወዳጅነት አላት፡፡ እስከተዘጋበት ጊዜ ድረስም በኪንሻሳ ኤምባሲ ነበራት፡፡ የሃገሪቱን ሰላም በማስከበር ሂደት የላቀ ድርሻ ከተወጡ የሃገሪቱ የቁርጥ ቀን ወዳጆች መካከልም ናት፡፡
በቅርቡ ለስራ ጉብኝት በሚል ወደ ኪንሻሳ አቅንተው የነበሩት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከቀጣዩ የህብረቱ ሊቀመንበር እና የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ጋር በግድቡ የድርድር ሂደት እና የሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡