በማዕከላዊ አውሮፓ ሀገራት በተከሰተው ጎርፍ የሟቾች ቁጥር መጨመሩ ተሰማ
ከሁለት አስርተ አመታ ወዲህ አስከፊው ነው በተባለው የጎርፍ አደጋ 4 ሀገራት ጉዳት ደርሶባቸዋል
በፖላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክ ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ አካባቢዎች በአደጋው ክፉኛ ተጎድተዋል
በማዕከላዊ አውሮፓ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በጣለ ከባድ ዝናብ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
እስካሁን በአደጋው የ15 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን የነፍስ አድን ሰራተኞች እና ወታደሮች የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ በነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡
ኦስትሪያ እና ሮማኒያ በርካታ የሰው ህይወት ያለፈባቸው ሀገራት ሲሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል፡፡
ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው የወንዞች ውሀ ሙላት ድልድይ እና የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ክፉኛ ጉዳት በማድረሱ የነፍስ አድን ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአካባቢው መሰል አደጋ ሲከሰት ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ ከፍተኛው ነው በተባለለት አደጋ በቼክ ሪፐብሊክ እና ፖላንድ ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ አካባቢዎችን ማጥለቅለቁ ነው የተነገረው፡፡
ከሎደዝኮ በተባለችው የፖላንድ የድንበር ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በግማሽ ተቋርጧል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ እንዳሉት አሁን ላይ ውሀው እየጎደለ ቢሆንም በአካባቢው የሚገኙ ዜጎች የንጽህ መጠጥ ውሀን ጨምሮ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኝ ሆስፒታል በጎርፉ በደረሰበት ጉዳት ነፍሰጡር ሴቶችን፣ አረጋውያንን እና ታካሚዎችን በጀልባ ወደ ሌላ ስፍራ እንዲጓጓዙ አድርጓል፡፡
በተመሳሳይ በቼክ ሪፐብሊክ ከዋና ከተማዋ 230 ኪሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ከተማ 70 በመቶ በውሀ ተሸፍናለች በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የተኛው ውሀም ጥልቀቱ ሁለት ሜትር እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
በአደጋው የመኖርያ ቤቶች ፈራርሰዋል፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ሲዘጉ የስልክ፣ የውሀ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ነው የተሰማው
የፖላንድ መንግስት አደጋው በደረሰባቸው ስፍራዎች የአደጋ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን በጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ 1 ቢሊየን ዝሎቲ ወይም 260 ሚሊየን ዶላር በጅቷል፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ተስክ በጎርፍ አደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው የጎረቤት ሀገራት ጋር እየተወያዩ እንደሚገኙ እና ከአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ በጋራ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡
የስሎቫኪያ እና የሀንጋሪ ዋና ከተሞች ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ይህን ተከትሎም ሀንጋሪ ለአደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ 12 ሺህ ወታደሮች በተጠንቀቅ አዘጋጅታለች፡፡