የሩሲያ እና የቻይና የጦር መርከቦች የሚሳይል ተኩስ ልምምድ አካሄዱ
ይህ ልምምድ ሁለቱ ሀገራት "ኦሽን-2ዐ24" ሲሉ የሰየሙት ልምምድ አካል ነው ተብሏል
በዚህ ልምምድ በሩሲያ በኩል የፓሲፊክ ባህር ኃይል ምድብን ጨምሮ ከ15 በላይ የጦር መርከቦች ተሳትፈዋል
የሁለቱ የእስያ ኃያላን ሩሲያ እና ቻይና የጦር መርከቦች የሚሳይል ተኩስ ልምምድ እያደረጉ ነው ተባለ።
የሩሲያ የፓሲፊክ ባህር ኃይል ምድብ የጦር መርከቦች እና የቻይና የባህር ኃይል በጃፓን ባህር የሚሳይል እና የከባድ መሳሪያ ልምምድ እያካሄዱ ነው። ይህ ልምምድ ሁለቱ ሀገራት "ኦሽን-2ዐ24" ሲሉ የሰየሙት ልምምድ አካል መሆኑን ሮይተርስ የሩሲያውን ሪያ ዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደዘባው ከሆነ በዚህ ልምምድ በሩሲያ በኩል የፓሲፊክ ባህር ኃይል ምድብን ጨምሮ ከ15 በላይ የጦር መርከቦች ተሳትፈዋል።
ባለፈው ሳምንት የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከሶቬት ህብረት መፈራረስ ወዲህ ከቻይና ጋር በመሆኑን የሚያደርጉትን ግዙፍ ልምምድ ባስጀመሩበት ወቅት አሜሪካ በእስያ ሞስኮን ለመብለጥ ሙከራ እያደረገች ነው የሚል ማስጠንቀቂያ አስምተዋል።
ፑቲን 'ኦሽን-2024' የተባለው ይህ ስትራቴጂካዊ ልምምድ ከሜዲትራኒያን ባህር እስከ ፖስፊክ ያለውን ቦታ እንደሚሸፍን እና የባህር ኃይል ዩኒቶችን የመዋጋት አቅም እና የጦር መሳሪያ አጠቃቃም የመፈተሽ አላማ እንዳለውም መግለጻቸው ይታወሳል።
ልምምዱ ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ካለው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የተገኙ ልምዶችንም ተካተውበታል ተብሏል። "ከወዳጅ ሀገራት ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥተናል" ሲሉ ፑቲን ልምምዱ በተጀመረበት ወቅት ለባለስልጣናት ተናግረዋል።
"በአሁኑ ወቅት እያደገ ከመጣው የጂኦፖለቲካ ውጥረት አንጻር ሲታይ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። አሜሪካ የትኛውንም ዋጋ ከፍላ ያላትን አለማቀፋዊ የወታደራዊ እና የፖለቲካዊ የበላይነት ለማስጠበቅ እየሞከረች ነው" ብለው ነበር ፑቲን።
ፑቲን በዋሽንግተን ቀስቃሽነት አለምአቀፍ የጦር መሳሪያ ማምረት ፉክክር ስለተፈጠረ ሩሲያ ለየትኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆን እንዳለባት እና የባህር ኃይሏን ማጠናከሯን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ፑቲን እንዳሉት "ከሩሲያ የሚቃጣ ስጋት አለ በሚል ሰበብ እና ቻይናን ባለችበት ለማስቆም፣ አሜሪካ እና አጋሮቿ በሩሲያ ምዕራባዊ ድንበር አቅራቢያ፣ በአርክቲክ እና በእስያ ፓሲፊክ ቀጣና ወታደራዊ ስምሪታቸውን ጨምረዋል።"
"አሜሪካ እና አጋሮቿ የአጭር ርቀት እና የረጅም ርቀት ሚሳይሎቻቸውን ሩሲያን ለማጥቃት በሚያስችል ርቀት ላይ ለማጥመድ እቅድ እንዳላቸው በግልጽ ተናግረዋል።"
አሜሪካ በበኩሏ በፓሲፊክ ቀጣና ያላት አጋርነት ቀጣናውን ለማረጋጋት እና ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው ማለቷ ይታወሳል።
ፑቲን ግን ይህ የአሜሪካ እንቅስቃሴ በቀጣናው ያለውን የኃይል ሚዛን ለማዛባት ነው ይላሉ። በዚህ ልምምድ ላይ አራት የቻይና መርከቦች እና 15 አውሮፕላኖች መሳተፋቸው ተገልጿል።