በናይጄርያ የተከሰተውን ጎርፍ ተከትሎ ከ200 በላይ እስረኞች አመለጡ
ቦርኖ በተባለው ክልል በደረሰው የጎርፍ አደጋ 229 ሰዎች ሞተዋል
የተመድ የስደተኞች ኤጄንሲ አደጋው ከ30 ዓመታት በኋላ አስከፊው ነው ብሏል
በናይጄርያ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 274 እስረኞች ከእስር ቤት አምልጠዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ቦርኖ በተባለው ክልል ባጋጠመው አደጋ በእንስሳት ማቆያ ውስጥ ባደረሰው ጉዳት አዞ እና እባብን ጨምሮ ሌሎች አደገኛ እንስሳቶች ወደ ሰዎች መንደር ስለመግባታቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የናጄሪያ የማረሚያቤት አገልግሎት ይፋ ባደረገው መረጃ ጎርፉ የእስር ቤቶችን ግድግዳዎች እንዲፈራረርሱ አድርጓል።
በዚህ የተነሳ እስረኞቹን ወደ ሌላ ስፍራ ለማጓጓዝ እየተደረገ በነበረ ጥረት 281 እስረኞች ያመለጡ ሲሆን ፖሊስ ባደረገው ጥረት ሰባት እስረኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የማረሚያ ቤት አገልግሎቱ ቃል አቀባይ አቡበከር ኦማር ያመለጡት እስረኞች አሻራ እና ማንነት መረጃ ለህዝቡ በማሰራጨት ፖሊስ የአደን ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባሰላፍነው ሳምንት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ እስካሁን የ229 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 386 ሺህ ያህሉ ደግሞ ከመኖርያቸው ተፋናቅለዋል።
በአደጋው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መጠፋታቸው የተነገረ ሲሆን የነፍስ አድን ስራዎች አሁንም ቀጥለዋል።
በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ እና መንደሮችን ከቦ በሚገኝው ከፍተኛ መጠን ያለው ውሀ የተነሳ የእርዳታ ሰራተኞች በጀልባ በመጓጓዝ ምግብ እና ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ አደጋ ከሞቱት እና ከተፋነቀሉት ሰዎች በተጨማሪ ከ25 ሺህ በላይ መኖርያ ቤቶች በውሀ መዋጣቸው ወይም መፍረሳቸው ሲሰማ 110 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ጉዳት ደርሶበታል።
ሰሜን ናይጄርያ በተደጋጋሚ በጎርፍ ከሚጠቁ አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳል ከአንድ ወር በፊት የሀገሪቱ ሜትሮሎጂ ኤጄንሲ የኒጄር ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በተመሳሳይ የተለያዩ አለም አቀፍ የአየር ትንበያ እና ሜትሮሎጂ ድርጅቶች በአፍሪካ በቀጣዮቹ ወራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚያስከትላቸው ተደጋጋሚ አደጋዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ።
በ2022 በአህጉሪቱ በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች የ500 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 1.4 ሚሊየን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጄንሲ በናይጄርያ የጎርፍ አደጋ ታሪክ ከ30 አመታት ወዲህ አስከፊው ነው ብሏል።